በህገወጥ ደላሎች ተታለው ከሀገር ሊወጡ የነበሩ 54 ሰዎች ተያዙ

98

ጎንደር መጋቢት 6/2011 በህገወጥ ደላሎች ተታለው ወደ ጎረቤት ሃገር ሱዳን ሊወጡ  የነበሩ 54 ሴት ወጣቶች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ወጣቶቹ የተያዙት ከኦሮሚያና ደቡብ አካበቢዎች በመንቀሳቀስ ጎንደር ከተማ እንደደረሱ መሆኑን የከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ቡድን መሪ ምክትል ኮማንደር አልማዝ ላቀው ዛሬ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በጎንደር ከተማ ወጣቶችና የፀጥታ አካላት ትብብር የተያዙት ወጣቶቹ በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ለመውጣት አስበው እንደነበር ለፖሊስ በሰጡት ቃል  ማወቅ ተችሏል፡፡

ወጣቶቹ የተያዙት ኮድ 3- 27162 አ.አ. በሆነ የጭነት አይሱዙ ተሽከርካሪ  በሸራ ታፍነው እንደሆኑ ያመለከቱት ቡድን መሪ  በነበረው መጨናነቅ ምክንያትም ራሳቸውን የሳቱ ስምንት ሴቶች የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ እንደተደረገላቸው አስረድተዋል፡፡

አሽከርካሪው መኪናውን ጥሎ ለጊዜው ቢሰወርም ፖሊስ ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ከተያዙት መካከልም እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ እንዳሉበትም ምክትል ኮማንደሯ አመልክተዋል፡፡

በዚህ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሳተፉ ደላላዎችን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ወጣቱ ወንጀል ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከተዘዋዋሪዎች መካከል ከወላይታ ልዩ ቦታው ስንቄ ከተባለ ስፍራ የመጣቸው ወጣት ታመነች ከበደ በሰጠችው አስተያየት  ከመነሻዋ ለደላላ 15 ሺህ ብር ከፍላ እንደመጣች ተናግራለች፡፡

ሱዳን ከደረሰች በኋላ ቀሪ 15 ሺህ ብር ለመክፈል እንደተስማማችም ጠቁማለች፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ባኮ አካባቢ የመጣቸው ወጣት መስካዩ ቡልተማ በበኩሏ ቤተሰብ በአራጣ ተበድሮ ለስራ በሰጧት 20 ሺህ ብር ለደላላ በመክፈል ጎንደር መድረሷን ተናግራለች፡፡

ከአዲስ አበባ ባህርዳር በአነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ካደረሳቸው  በኋላ በጨለማ በጭነት መኪና ወደ ጎንደር እንዳመጧቸውም አመልክታለች፡፡

ዛሬ እኩለ ቀን በከተማው ቡልኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተያዙት እነዚህ  ወጣቶች የመጡበትን በማጣራት ወደየቤተሰቦቻቸው ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመሩም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም