በድጋፍ እጦት ወደ ሥራ ልንገባ አልቻልንም — በአምቦ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች

432

አምቦ መጋቢት 6/2011 በማህበር ተደራጅተን አስፈላጊውን መስፈርት ብናሟላም የገንዘብ፣ የብድርና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ በማጣታችን ወደ ሥራ መግባት አልቻልንም ሲሉ በአምቦ ከተማ ወጣቶች ገለፁ።

የወጣቶቹን ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።

በከተማው የቀበሌ 02 ነዋሪ ወጣት ደምሴ ፍሮመሳ ለኢዜአ እንደገለፀው ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ከአራት ወር በፊት ተደራጅተው  በእንጨት ስራ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ዝግጅት አድረገዋል።

በመስፈርቱ መሰረት የሥራ ዕቅድ አዘጋጅተው 500 ሺህ ብር ብድር ለማግኘት የሚጠበቅባቸውን 45 ሺህ ብር መቆጠባቸውንም ተናግሯል።

ይሁንና የገንዘብ ብድርና የመስሪያ ቦታ ባለማግኘታቸው ወደ ሥራ ሳይገቡ መቅረታቸውን ነው ወጣት ደምሴ የገለጸው።

ወጣት መሰረት ፊጣ በበኩሏ ከአራት ወር በፊት ከስድስት ጓደኞቿ ጋር ተደራጅተው በምግብ ንግድ ሥራ ለመሰማራት የሚያስፈልጋቸውን መስፈርት አሟልተው ለአስተዳደሩ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሳለች።

” የብድር ገንዘብና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ በማጣታችን ወደ ሥራ ሳንገባ ቀርተናል” ስትልም ቅሬታዋን ገልጻለች።

“ወደ ሥራ ባለመግባታችን ትምህርታችንን አጠናቀን ዛሬም ከቤተሰብ ጥገኝነት አልተላቀቅንም ” ያሉት ወጣቶቹ የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል።

በአምቦ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና ህጋዊ ሥራ ማረጋገጫ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዘውዴ እጅጉ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የወጣቶቹ ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አምነው አስተዳደሩ ጥያቄውን ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘንደሮ በሥራ አጥነት ከተመዘገቡ 4 ሺህ 948 ወጣቶች መካከል 3ሺህ 889 የሚሆኑት የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ገንዘብ፣ 65 የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች እንዲሁም 36 ሄክታር የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ እዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ለወጣቶቹ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ነው የገለጸው።

በመስሪያና በመሸጫ ሼዶች እንዲሁም በመስሪያ ቦታ እጥረት ምክንያት ሁሉንም ወጣቶች ወደ ሥራ ለማስገባት አለመቻሉን ተናግረዋል ።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ተደራጅተው የሚጠበቅባቸውን መስፈርት ያሟሉ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶችን በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራቶች ወደ ስራ ለማስገባት በዘርፉ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተሰራ ነው።