ጉዞ ከሸዋ-አድዋ (ክፍል ፪)

579

አየለ ያረጋል (ኢዜአ)

የአገር ፍቅር እንጂ ገበሬውስ ምርቱን አልሰበሰበም። የመኸር ሰብል አልደረሰም፤ ወርኅ ጥቅምት ነውና። ንጉሠ ነገስቱ ‘ጠላት ድንበር አልፎ፣ መሬት እንደ ፍልፈል እየቦረቦረ ነውና ክተት’ ያሉት ሰራዊት ወሎ ደርሷል። ‘ወደ አድዋ እንሂድ ካለ፣ አይቀርም በማርያም ስለማለ’ እንዲል ዘፋኙ የአድዋ ዘማች በሶስት ቦታ ክተት ተጠራ። በዚህም የመሃል አገሩ የንጉሠ ነገስቱ ጦር ወረኢሊ (ደቡብ ወሎ)፤ የጎጃም፣ የበጌምድርና አካባቢው ጦር  አሸንጌ (ራያ)፣ የስሜን፣ ወልቃይትና ጠገዴ ጦር መቀሌ ተጠራ። እንደ ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ማስታወሻ ድንኳን ተካይ፤ ዕንጨት አቅራቢው፣ ወጥ ሰሪው፣ እንጀራ ጋጋሪው፣ እህል ውሃ ተሸካሚው፣ መልከኛው (አራጁ)፣ በቅሎ ጫኙ፤ ተዋጊው ሁሉም በየፊናው እንስሳቱም ሳይቀር ተደራጅቶ ዘመተ። የዘመቻው ግብር ሳይጓደል መድረሱን ሲገልጹ “በ፮ ድንኳን እንጀራው ሲጋጋር ሲያድር፣ በ፬ ድንኳን ወጡ ሲሰራ ሲያድር፣ ጠጁ በቀንድ፤ በኮዳ ፫ መቶ፣ ፮ መቶ በሚሆን ገንቦኛ ሲጓዝ ሲያድር ግብሩ የጎደለ ይመስልሃልን” ይላሉ። ከራስ (በኋላ ንጉስ) ወልደጊዮርጊስና ደጃዝማች (በኋላ ራስ ቢትወዳድ) ተሰማ ከግዛታቸው የቦታ ርቀት ሳቢያ እንዲሁም ዘውድ እንዲጠብቁ ከቀሩት ራስ ዳርጌ በቀር ሁሉም መኳንንት ጦሩን ይዞ ዘምቷል። (ከአድዋ ዘመቻ የቀሩት ራስ ወልደጊዮርጊስና ደጃዝማች ተሰማ በአድዋ ዘመቻ ዋዜማ በጣሊያን የጎንዮሽ ድጋፍ አመጽ ያነሳነውን የአውሳውን (አፋር) ባላባት መሃመድ አንፋሪን ጦር ቁጥጥር ስር በማዋል ሌላ አገራዊ ቀውስ አክስመዋል)።

የምኒልክ ጦር ጥቅምት 2 ቀን ከአዲስ አበባ ተነስቶ በ18ኛው ቀን ነበር ወረኢሉ የገባው። ‘ከሰማይ የወረደ በረዶ እንጂ ሰራዊት አይመስለም ነበር የጦሩ ብዛት’ ይላሉ የስፍራው አባቶች የሰሙትን ሲናገሩ። ንጉሠ ነገስቱ ወረኢሉ ላይ ራስ ሚካኤልን፣ ራስ ወሌን፣ ራስ ቢትወደድ መንገሻን፣ ራስ መኮንንን፣ ራስ አሉላን፣ ዋግሹም ጓንጉልን፣ ደጃች ወንዴን፣ ፊታውራሪ ገበየሁን፣ ፊታውራሪ ተክሌን፣ ሊቀ መኳስ አድነውን፣ ቀኛዝማች ታፈሰን አስቀድመው ላኩ፤ ‘ጣሊያን ከመጣ ውጉት፣ ካቀታችሁ ላኩብኝ’ አሏቸው። በሌላ በኩል ንጉሡን የሸኙት አባጅፋርን፣ ደጃች ጆቴን፣ ካዎ ጦናን አገሬን ጠብቁ ብለው ከወረኢሉ መለሷቸው። እርሳቸውም ወረኢሉ ሰንብተው፣ ደሴ፣ ተሁለደሬ፣ ውጫሌ፣ አሸንጌ፣ ማይጨው… እያሉ ወደ አድዋ ዘመቱ።

ወረኢሊ የዳግማዊ ምኒልክ ተወዳጅ ከተማ ናት። የአማታቸው የአብቸው በያን (የልጃቸው የንግስተ ነገሰታት ዘውዲቱ እናት) አገርም ናት። ከደሴ ከተማ በስተምዕራብ 76 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ወረኢሉ ለአድዋ ዘመቻ ጦር ማዕከል ብቻ አይደለችም። ከአድዋ ዘመቻ በፊት የትግራይ ባላባቶችን ለማስገበር ሲዘምቱ አርፈውባታል። ንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግስት ሰርተውባታል፤ ችግኝ ተክለውባታል። (‘አባ ግንባሩ’ ተብሎ የሚጠራ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተከሉት እድሜ ጠገብ ዛፍ ዛሬም በስፍራው አለ)። ለበርካታ መኳንንቶች በመኖሪያነት ያገለገለች ቦታ ናት። በወቅቱ ሊቀ ጳጳስ በአቡነ ማቴዎስና በአፄ ምኒልክ አጎት በራስ ዳርጌ ስም የሚጠሩ ሰፈሮች ይገኛል። (በነገራችን ላይ በከተማ ዕድሜ ጠገብ ባለጭቃ ፎቅ ቤቶች ሞልተዋል፤ በገጠር አካባቢም ቤቶችን በፎቅ የመስራት ባህል ይበዛል)። በ123ኛው ዝክረ አድዋ ሲከበር ወደ አድዋ ያመራው ልዑካን ከጎበኛቸው ታሪካዊ ስፍራዎች ወረኢሉ አንዷ ነበረች። ወረኢሉ ከተማ (ወረዳዋም በስሟ ይጠራል) ወይናደጋ አየር ንብረት አላት፤ ሰሜን ሸዋና በሌሎች የደቡብ ወሎ ወረዳዎች የተሳሰረች የንግድ ስትራቴጂ ስፍራ ናት። ከስፍራው ባገኘሁት መረጃ መሰረት ጥንታዊ ስሟ ‘ምድረ ሐጓ’ ነበር፤ ‘ዋስል’ ተብላም ትጠራ ነበር። የቤተ አምሃራ መነሻ ናት ይላሉ። ከኦሮሞ ነገዶች አንዱ ከሆነው ከወሎ ነገድ የሚወለደው የ’ኢሉ’ አገር ስለሆነች ‘ወረ-ኢሉ(በኦሮምኛ የኢሉ መንደር) መባሏን ይናገራሉ። ወረኢሉ በ1860 ምኒልክ በከተማነት ቢቆረቁሯትም ከላሊበላ ቀጥሎ የስልጣኔ ስፍራ እንደነበረች የከተማዋ አባቶች ያምናሉ። ከ1190 እስከ 1228 ዓ.ም በነበረው የአፄ ነአኩተ ለአብ ዘመነ መንግስት እንደተቆረቆረች ይገለጻሉ። ‘ወረኢሉ የቤተ አምሃራ መናገሻና የ12ኛው ክፍለ ዘመን የስልጣኔ መነሻ ናት’ በማለት እንደ ማሳያ የደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንና የመካነ ስላሴን ያነሳሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአሰራሩ ለየት የሚለው ከ1485 እስከ 1524 የመካነ ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ታንጿል። በአዔ ናዖድ መሰረቱ ተጥሎ በአጼ ልብነ ድንግል የተጠናቀቀው የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ፖርቱጋላዊ ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝም ጽፎለታል። የግራኝ አሕመድ ታሪክ ጸሐፊ ዓረብ ፋቂህ  “በዚህ በቤተ አምሃራ በሐበሻ ምሳሌ የሌላት አንዲት ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡ እርሷን የሠራት የወናግ ሰገድ /ልብነ ድንግል/ አባት ንጉሥ ናዖድ ነው፡፡ የእርሷ ሥራና ጌጥ 13 ዓመት ፈጀበትና ሳይጨርሳት ስለ ሞተ ልጁ ወናግ ሰገድ ከአባቱ አስበልጦ 25 ዓመት ሙሉ አሠርቶ አስጨረሳት፡፡ ሁለመናዋ በወርቅ የተለበደ ስለሆነ እንደ እሳት ታንጸባርቃለች፤ በውስጧ ያለው ጻሕል፣ ወሰንና ብረት የወርቅና የብር ነው፡፡ ስፋቷ መቶ ክንድ ቁመቷ ግን ከመቶ ሃምሳ ክንድ ይበልጣል፡፡ ሁለመናዋ በጌጠኛ ዕንጨትና ድንጋይ በወርቅና በከበረ ድንጋይ የተለበደ ነው፡፡ ስሟ በክርስቲያኖች ቋንቋ መካነ ሥላሴ ትባላለች፡፡ … በዚህች ቤተ ክርስቲያን የዘርዓ ያዕቆብ የልጅ ልጅ የአድማስ ሰገድ /በእደ ማርያም/ ልጅ የናዖድ መቃብር አለ” ብሎ ጽፏል። መካነ ሥላሴ በግራኝ አህመድ ተቃጥሏል። በአሁኑ ሰዓት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የአርኪዮሎጂ ጥናት ማዕከል ሆኗል።

ሌላው በተለይም ከአድዋ ጋር ትልቅ ታሪክ ያለው የወረኢሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ነው። በ1220 ዓ.ም በአጼ ናኩቶለአብ ዘመነ መንግሰት የተመሰረተው የደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከግራኝ አህመድ ቃጠሎ አላመለጠም። በአፄ ገላውዲዮስ፣ በአፄ ዮሐንስና በአጼ ምኒልክ በተለያዩ ጊዜያት ታድሷል። አሁን ላይ የሚገኘው ግዙፍ ቤተ ክርስቲያን በተመረጡ በአገር በቀል እንጨቶች በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተሰራ ሲሆን የአሰራር ጥበቡም የሚደነቅና በስዕላት ያሸበረቀ ነው (ስዕላቱን የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ አጎት (ራስ ሀብተማርያም በያን) ያሳሉት ነው)።

የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ ቀሲስ አንተነህ ለዑልሰገድ ለኢዜአ ዘጋቢ እንደገለጹለት፤ ደብረ ሠላም ቅዱስ ጊዮርጊስ የአደዋ ዘማች ነው። ቤተ ክርስቲያኑ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱና ንግስት ዘውዲቱ ጨምሮ የተለያዩ መኳንንት የስጦታ እቃዎች፣ ነዋያ ቅድሳት ለአብነትም ጥንታዊ ብራና መፅሐፍት፣ የምኒልክ የንግስ አክሊል፣ የዘውዲቱና ጣይቱ ስጦታዎች፣ ባለወርቅ መርገፍ ጥላዎች፣ የብር ዋንጫዎች፣ የብር መስቀሎች፣ የብርና ወርቅ ለምዶች፣ አድዋ ዘማች ስዕለ ጊዮርጊስ፣ ከወርቅና ብር የተሰሩ ፅዋ፣ ፅና እና ሌሎች ነዋየ ቅድሳት ይገኛሉ። በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ውስጥ የራስ ሀብተማርያም እና ቤተሰባቸው መቃብር በድንጋይ ጠርብ በልዩ ጥበብ ሰርቶ ግቢው ውስጥ ይገኛል። ሌላው አስገራሚ ነገር ታዲያ ከመቃብር ቤቱ ህንፃ ግድግዳ ላይ የሁለቱን ኃይማኖት (ኦርቶዶክስና እስልምና) ወዳጅነት ለማሳየት መስቀል እና ጨረቃ በጋራ ተቀርጾ ይስተዋላል። ሰው በሕይወት አልፎም መቻቻሉን ለማሳየት በተግባር ያስቀረጹበት ስራ። በፋሽስት ኢጣሊያኖች ወረራ ቤተ ክርስቲያናትና ቅርሶችን ማውደም ቀዳሚ ስራው ነበር። ቀሲስ አንተነህ “ፋሽስት በአድዋ ወቅት ያጋጠመውን አውቆ በሁለተኛው ወረራ (በ1928)ቱ ጥፋት እንዳይደርስበት የሳር ክዳን የነበረውን ቤተ ክርስቲያን ገፈው በላሜራ(ቆርቆሮ) ለወጡት። ከነፃነት በኋላ ግን አባቶች ‘የጠላት ገንዘብ አባታችን ላይ አይሆንም’ በሚል ላሜራውን ገፈው ቆርቆሮ አለበሱት” ይላሉ)። ምናልባትም ፋሽስት የተንከባከበው ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን አይቀርም። በ1980ዎቹ አጋማሽ ጥፋትና ዘረፋ ደርሶበታል። የንግስት ዘውዲቱ የወርቅ አክሊል፣ የወርቅ ከበሮ፣ የወርቅ መስቀል ጨምሮ ብዙ ቅርሶች ተዘርፈዋል። አሁን ያሉት ትርፍ ናቸው የሚሉት ቀሲስ አንተነህ፤ አሁን የቀሪ ውድ ቅርሶችም ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ እንደሌላቸው ይገልጻሉ። ቤተ ክርስቲያኗም ሙዚየም ገንብታ ጥበቃ ለማድረግ አቅም እንደሌላት ገልጸው፤ በእርጅና ምክንያት እየነተቡ ያሉ ቅርሶችን ለመጠበቅና ከዘረፋም ለመከላከል ድጋፍ እንደምትሻ ይገልጻሉ።

የከተማዋ ከንቲባ አቶ እሸቱ ታረቀኝ “ባለፉት 27 ዓመታት ይሄ አገር፤ ይሄ ህዝብ እያልን አድዋን ስንዘክር የዳግማዊ ምኒልክን ስም አናነሳም ነበር።ይሄን ይቅርታን እየጠየቀን ነው፤ ባለታሪኮችን ባለማንሳት” ይላሉ። ለተለያዩ የወረዳ ቢሮዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው በስፍራው የሚገኘው የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተ መንግስትን አሳድሰን ቅርስነቱን ለመጠበቅ ታቅዷል” ብለዋል። አድዋ ሲነሳ ወረኢሉ አብራ ሳትዘከር መቆየቷን ይገልጻሉ። “ስሟን ለማደስና የዳግማዊ አጼ ምኒልክን ታሪክ ለማስታወስ የአፄ ምኒልክ ሀውልት ለመገንባት፣ ተቋማትን በስማቸው ለመሰየም እንቅስቃሴ ጀምረናል” ብለዋል። ቅርሶችን ከጉዳት ለመጠበቅም ሙዚየም ለመገንባት ዝግጅት መጀመሩን አንስተዋል። የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ሲታሰብ ለጦርነቱ መንስኤ የሆነው የውጫሌ ውል የተፈረመበት ‘ይስማ ንጉስ’ እና የጦር ማደራጃ ለነበረችው ‘ወረኢሉ’ መታሰብ እንዳለባቸው የሚገልጹት አቶ እሸቱ፤ ”በሁለቱም ስፍራዎችም ዩኒቨርሲቲው ቅርንጫፍ እንዲኖረው እየጠየቅን ነው” ብለዋል። ‘ማህደረ ወረኢሉ’ የተሰኘ መጽሃፍ በቀጣይ ዝክረ አድዋ ለማሳተም መታቀዱንም ጨምረው ይገልጻሉ። ወረኢሉን ለቀን ስንወጣም እንዲህ በምኞት ተሰናበትኳት።

የላልይበላ ፈለግ አሽታች፤ የአፄ ናኩተለአብ መሠረት፣

የቤተ አምኃራ ክፋይ፤ የይኩኖአምላክ ንጉሠ አምኃራ ርስት፣

የወሎ ትውልድ ‘አገረ ኢሉ’፤ የወጭ ወራጁ መስፍን ጎዳና ታሪካዊት፣

የአማቱ አብችው በያን፤ እመ ዘውዲቱ ምኒልክ አገረ ግዛት፣

ወረኢሉ የቀድሞዋ ‘ምድረ ሐጓ’፤ የምኒልክ ቁርቁር፤ ውድ ከተማ

የጦሩ ማዕከል የአዋጁ ክተት ማማ፣

ወረኢሉ ግራ ቀኝ መመልከቻ፤ ተስፈኛዋ ከተማ፣

ነፋሻማዋ ለምለም ምድር፤ በአፍቃሪሽ ታላቁ የጥቁር ንጉሥ ስም ታሪክሽ ይሰማ!!

‘የነጻነት ቀን ሳይሆን የድል ቀን የምታከብር ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ናት’ ይላሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አባተ ጌታሁን። በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ቀያሪው የአድዋ ጦርነት መንስኤ የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ነው። ይህ ውል የተፈረመበት ቦታም ይስማ ንጉስ ነው። ታሪካዊ ስፍራውን ለቱሪስት መዳረሻነት ለማልማት በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም አማካኝነት የይስማ ንጉስ የባህል ማዕከል ግንባታ ተጀምሯል። (የዳግማዊ ምኒልክን ጨምሮ የውሉ ተዋናዮችን ሐውልት እንደሚገነባ ቢነገርም እስከካሁን ምንም ነገር የለም)። ከደሴ- ወልድያ መስመር 40 ኪሎሜትር በአምባሰል ወረዳ ይገኛል። በአምባሰል ወረዳ ይስማ ንጉስን ጨምሮ በወረዳው በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች ቢኖሩም መንገድን ጨምሮ መሰረተ ልማቶች የሉም። ይሰማ ንጉስ ለመድረስም ከዋናው መንገድ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ቢሆንም መንገዱ ዛሬም ባለመስተካከሉ ምቹ አይደለም። በአማራ ህንፃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የሚሰራው ይስማ ንጉሥ የባህል ማዕከል ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የቴክኒክ ማኔጀር ኢንጂነር ዮሐንስ አሰፋ እንዳሉት፤ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም የተጀመረው የባህል ማዕከሉ ግንባታ 52 በመቶ ደርሷል። ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይናገራሉ። ማዕከሉ ግንባታ ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የሚገነባ ሲሆን በጥቁርና ነጭ ቀለም (አሸናፊውን ጥቁርና ተሸናፊውን ነጭ ለመግለጽ) ይኖረዋል። አሸናፊነትን የሚያመለክት የእጅ ምልክትም በማዕከሉ ጣሪያ ላይ ይኖረዋል፡፡ የውሉን አንቀጽ ለማስታወስም ከባህል ማዕከሉ ዋና መግቢያ በር ላይ የግዕዙ ‘፲፯’ ቁጥር ይኖረዋል። የባህል ማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያሳዩ መረጃዎችን የሚይዝ ሙዚየምና ለጎበኝዎች አገልግሎት የሚሰጥ ካፍቴሪያም ይኖረዋል እንደ ኢንጂነር ዮሐንስ ገለጻ።

ከውጫሌ ቀጥሎ ወደ ማይጨው ታሪካዊ ስፍራ ደርሰናል። ከአዲስ አበባ 666 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ማይጨው ከ1888 እስከ 1928ቱ የኢትዮ ጣሊያን ጦርነት ታሪኮችን ይዛለች። ፀሃፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ‘ታህሳስ 5 ቀን 1888 ዓ.ም አላማጣን አልፈው ኦፍላ (ኮረም) ደረሱ፤ በ8ኛው ቀን አሸንጌ ባህሩ ዳር ሰፈሩ’ በማለት ፅፈዋል። የነጉሠ ነገሥቱ ጦር ማይጨው በነበረበት ወቅት የከብት በሽታ ገብቶ ፈረሱ፣ በቅሎው መሞቱን ይናገራሉ። በዚህም ንጉሱ እንዳይመለሱ ጠላት ወደመሃል አገር እየገሰገሰ፣ ጉዞውን እንዳይቀጥሉ የገባው በሽታ አስቸጋሪ ሆነባቸው። በገዳሟ ቅጥር ግቢ ያገኘኋቸው መምህር ከበደ ባራኪ “በአካባቢው ተወላጅ የነበሩ ግራዝማች ህዊ የተባሉ ሰው ‘እዚህ አካባቢ ጸበል አለ። አቡነ ተክለሃይማኖት ነው የሚባለው፤ እኔ ሙስሊም ነኝ፤ ሰው ይፈውሳል ነው የሚለው፤ እርሱን አይተው እንደሁ’ ሲላቸው ንጉሱ ነገስቱ ወደ ፀበሉ አመሩ” ይላሉ። ንጉሱም ፀበል ለሰራዊቱና ለአጋሰሶቻቸው(በተለይም እንደመኪና የሚያገለግላቸው ዳኘው የተሰኘውን በቅሎ በመታመሙ) አጠጥተው በደህና ጉዟቸውን መቀጠላቸውን ይተርካሉ። በአጼ ኢያሱ ዘመነ መንግስት የተመሰረተችው ቤተ ክርስቲያኗንም ከዘመቻ ሲመለሱ በቃላቸው መሰረት ገደሟት፤ በአሁኑ ወቅት ደብረ ጽጌ ተክለሃይማኖት ገዳም ትባላለች። መምህር ከበደ እንዳሉት በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተገደመችው ደብረ ጽጌ ተክለኃይማኖት ገዳም ከ30 በላይ የብራና መጽሃፍት፣ የአጼ ምኒልክ ፎቶ፣ ሱሪ፣ ቀሚስ፣ የነገሰታት መስቀል፣ የነገስታት ደብዳቤዎች፣ ደወልና ሌሎች ቅርሶችን ይዛለች። ንጉሠ ነገስቱ ወደ አድዋ ሲሄዱና ሲመጡ ያረፉበትና የመንፈስ ስንቅ ያገኙበት ስፍራ ቢሆንም በዝክረ አድዋ ሁሌም ስሟ እንደማይነሳና እንደማይታወቅ ይናገራሉ።

የራስ መኮንን ጦር ጀግንነቱን ያሳየበት፣ ህመም ላይ የነበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ እንደ ዝንጀሮ ገደል ለገደል እየተዘዋወሩ ዘንግ ይዘው ያዋጉበት፣ ቀኛዝማች ታፈሰ በአንድ ጎራዴ የጠላት ሬሳ የከመረበት፣ ጣሊያናዊ ሜጀር ቶዝሊ የተገደለበት የአምባላጌ (አምባላጄ) ጦር ሜዳም ማይጨው አካባቢ ይገኛል። ከዚህ በላይ ደግሞ በማይጨው ጦርነት (መጋቢት 1928) ከ30 ሺህ በላይ አርበኞች ያለቁበት ሐውልትና አጽም ማይጨው ከተማ ይገኛል። በአግባቡ የተደራጀ ባይባልም የአርበኞቹ አጽም በደብረ ሰማዕት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ይገኛል። በዓለም ላይ በተከለከለ የመርዝ ጋዝ በአውሮፕላን ተርከፍክፎባቸው ያለቁ ኢትዮጵያዊያን አፅም ከነጻነት በኋላ (በ1933 ዓ.ም) በአጼ ኃይለስላሴ መታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው፣ አጽማቸውም አንድ ቦታ አረፈ። በደርግ ዘመን ግን ቦታው የወታደር ካምፕ በመሆኑ ተቀየረ። በኢህአዴግ ደግሞ ለስታድየም ቦታው በመፈለጉ የቤተ ክርስቲያኗ ሰበካ ጉባኤ አጽሙን ሰብስበው በክብር አስቀመጡት። የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አርበኞች አፅም በመሆኑ መንግስት የተጠናከረ ሙዚየም ሊገነባለት እንደሚገባ የወረዳው ቤተ ክህነት ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን ረዳኢ ሃለፎም ይናገራሉ። የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሀለፎም አካባቢው በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጸው፤ ነገር ግን መዳረሻዎችን የማልማት ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየው “አገሪቱ ካላት ሰፊ የቱሪዝም ሀብት አንጻር ነው” ይላሉ። ክልሉ በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ከባድ መስዋትነት የተከፈለበት ስፍራ በመሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማትና የአርበኞቹን አጽም ጨምሮ ታሪካዊ ሂደቱን የሚያስቃኝ ቤተ መዘከር ለመገንባት ስራ መጀመሩን ያብራራሉ።

የትግራይ ተራራማ መልክዓ ምድሮችን እያቋረጥን መቀሌ ከተማ ገብተናል። መቀሌ መግቢያ ላይ (አሁን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ) የሚገኘው እንዳ የሱስ የቅድመ አድዋ ጦር ሜዳ ነው። ብዙ ወታደሮች ያለቁበት፣ የበጅሮንድ (በኋላ ደጃዝማች) ባልቻ ሳፎና የሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧያለው መድፈኝነት (ራስ አባተ የጠላትን መድፍ በመድፋቸው ሰባብረዋል) የተመሰከረበት፣ ጠላትን እጅ ወደላይ ያስባለው የእቴጌ ጣይቱ ብልሃት የታየበት የመቀሌ ጦርነት ከዚሁ ነው። ጣሊያን በስፍራው የነበረውን የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ታቦቱን አውጥቶ ከባድ ምሽግ ሰራበት። በውጭም በግቢም መሬቱን እየቆፈረ ባሩድ ቀበረበት። እናም የኢትዮጵያ ሰራዊት ከጠላት ጋር ለመግጠም አስቸጋሪ ሆነ። በድፍረት የተጠጋው የራስ መኮንን ሰራዊት ለጠላት መስዋት ከመሆን በቀር ጠላትን ማስወጣት አቃተው። እቴጌ ጣይቱም ጠላት ውሃ የሚቀዳበትን ምንጭ (ማይ እንሽታይ) በብልሃት አስከበቡ። በዚህም የኢትዮጵያ ጦር 15 ቀን ሙሉ ሌት ተቀን እየተዋጋ ጠላትን ውሃ እስጠምቶ እጅ ወደላይ አስባለ። በኋላም በዳግማዊ ምኒልክ ቸርነት ከእርዱ (ምሽጉ) ወጥተው ወደ አዲግራት እንዲሄዱ ተደረገ። ጠላት በውሃ ጥም ምን ያህል ተቸግሮ እንደነበርና በውሃ ጥም እንዳለቀ ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ “ከዚህም በኋላ አጼ ምኒልክ ጣሊኖችን በማሯቸው ጊዜ በጅሮንድ ባልቻን ልከው ሰውም ከብቱም ውሃ ይጠጣ ብለው ለዘበኞች አዘዙ። ጣሊያኖችም ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ውሃም ሲወጡ ዘመዱን ለመገናኘት የናፈቀ ሰው ይመስላሉ። ከጠጣ በኋላ ብዙ አለቀ። አንዲቱም ውሻ በሩ ቢከፈትላት ሩጣ ወጥታ ከውሃው ደርሳ ዘበኞች ሶስት ጋሻ አጠጧት። ውሃውን ከጠጧች። ከጠጣች በኋላ ሁለት ሙት ወልዳ እዚያው ላይ ሞተች” ይላሉ። ባይፈቀድላቸው ኑሮ ምናልባትም በውሃ ጥም ያልቁ እንደነበር ታሪክ ይናገራል። ከምሽግ የወጣው የሜጀር ጋልያኖ ጦርም ከብቱ በውሃ ጥምና በመትረየስ አልቆበት ስለነበር በምኒልክ ፈቃድ የዕቃ መጫኛ አጋሰስ ተሰጥቷቸው ተሸኙ። በዚህ ድርጊትም ዳግማዊ የፍቅርና ርህራሄ ­ጥጋቸውን አሳዩ። (በምኒልክ ውሳኔ ግን የወቅቱ የወገን ሰራዊት ቅር ተሰኝቷል)። ዛሬ ላይ በስፍራው ላለቁ ጣሊያኖች መቃብር ተሰርቶ በክብር ይጎበኛል። በኢትዮጵያ በኩል ግን ለድል ከፍተኛ ሚና የተጫወተችው ‘ማይ እንሽታይ’ ስንኳ ለቱሪዝም መዳረሻነት ማልማት እንዳልቻለ ታዝበናል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ትግራይ ጦር ሜዳ ናት። ጠላት ‘እገባለሁ፤ አልገባም’ ግብግብ የትግራይ ተራሮች አብረው ተዋግተዋል። የትግራይ ህዝብ በየታሪክ ህዳጉ መከራን ተጎንጭቷል። ከመቀሌ አድዋ ሲሄዱ (በቆላ ተንቤን መንገድ) አብይ አዲ ትገኛለች። አብይ አዲ የንግስት ሳባ፣ የራስ አሉላ፣ የአጼ ዮሐንስ ትውልድ አገር እንደሆነች የአካባቢው አባቶች ያምናሉ። ከመቀሌ 90 ኪሎ ሜትር፣ ከአዲስ አበባ ደግሞ 875 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የቆላ ተንቤን ወረዳ ዋና ከተማዋ ‘አብይ አዲ’ የአጼ ሰርፀ ድንግል ዘመነ መንግስት የተቆረቆረች ጥንታዊት ከተማ ናት። ነዋሪዎችም በ’አውሪስና አሸንዳ’ በሚባሉ ባህላዊ ጭፈራ እሴቶች የታወቁ ናቸው።

አብይ አዲ ወደ ሽሬ፣ መቀሌ፣ ዲማ (ጎንደር)፣ አዲግራት(ሀውዜን)፣ ሰቆጣ፣ ተከዜ ሃድሮሊክ ፓወር የሚወስዱ መንገዶችን ያስተሳሰረች ከተማ ናት። ከከተማዋ ወደ አድዋ ወጣ ብለን ወርቅ አምባ ትገኛለች። ስፍራውን ያስጎበኙን መምህር መስፍን ወልደገብርኤል እንደሚሉት በ1928ቱ የኢትዮ-ፋሽስት ኢጣሊያ ጦርነት (ተንቤን ግንባር) የተደረገበት፣ በራስ ስዩም መንገሻና በራስ ካሳ ኃይሉ የሚመራው የኢትዮጵያዊ ጦር በአውሮፕላን መርዝ የተጨፈጨፈበት፣ በአምባላጌና በአድዋ የዘመቱት ዕውቁ አርበኛ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ በ1928ቱ ወረራ ጠላትን በአርበኝነት ሲያርበደብዱ ከርመው የተሰውበት አካባቢ፣ በሌላ በኩል 10 ሺህ 888 የጠላት ወታደሮች ያለቁበት ስፍራ ነው – ወርቅአምባ። ኢጣሊያ ከ150 ሺህ በላይ የጣሊያንና የአስካሪስ ሰራዊት ባሰለፈችበት በዚህ ጦር ግንባር በስፍራው ለተገደሉ ወታደሮቿ ጠላት ኢትዮጵያን ሳይለቅ ያሰራው መቃብር አለ። የጦር መሪዎችም ተራ ወታደሮቿም ማንነታቸው የታወቁና ያልታወቁ በስርዓት የተቀበሩበት መቃብር አለ። ከተቀበሩት መካከል በ1960ዎቹ አካባቢ አጽማችውን ለመውሰድ ተስማምተው 600ዎቹ የተወሰዱ ሲሆን ቀሪዎቹ ግን በወቅቱ በነበረው የተማሪዎች ተቃውሞ አጽማቸው እንዳይሄድ ተከልክሎ ዛሬም በስፍራው ይገኛል። ለሁለቱም አገሮች ስምምነት የአንበሳ ምልክት ያለበት የመታሰቢያ ሐውልትም ቆሟል። የኢትዮጵያዊያን ወገን ያለቁ ዜጎች ግን መቃብር የላቸውም፤ በርግጥ በየኮረብታው፣ በየገደሉ፣ በየሸለቆው ቢቀበሩም መሬቱ የአገራቸው አፈር ነው።

ከተንቤን ቀጥሎ ስመ ገናናዋ ‘አድዋ’ ደረስን። ገናና ታሪክ የተጻፈባቸው ተራሮች፣ የዛሬና የነገ ትውልድ በቅኝ ግዛት ቀንበር ትከሻው ጎብጦና አንገቱን ደፍቶ እንዳይኖር የክብር አክሊል ያቀዳጁ መልክዓ ምድሮች፣ በአባቶች ደምና አጥንት የከበሩ ስፍራዎችን ካቀፈችው አድዋ ደረስን። ከ123 ዓመታት በፊት በበርሊኑ የአፍሪካን የመቀራመት ጉባኤ ተገፋፍታ የመጣችው ኢጣሊያ አንገት የደፋችበት የታሪክ ሁነት የተፈጸመባቸው ስፍራዎች ታሪካዊ ስም እንጂ ታሪኩን የሚዘክር ነገር አልያዙም። የመቁሰል አደጋ ገጥሞት ጥላ ስር እናሳርፍህ ቢባልም ለጣሊያን አንድ እጅ ይበቃል በሚል ጠላት ሲያባርር የተሰዋው የ25 ዓመቱ ጀግና ቀኛዝማች ታፈሰ አባይነህ (የደጃዝማች ኃይለስላሴ ወንድም)፤ ዲፕሎማቱ ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ (የራስ ደስታና የደጃዝማች አበበ ዳምጠው አባት)፤ ከጣሊያን መድፈኞች መሃል ገብቶ በጀግንነት የተሰዋው ደጃዝማች ጫጫ፣ ደጃዝማች በሻህ አቦዬ(የንጉስ ወልደጊዮርጊስ ወንድም)፤ የፊታውራሪ ገበየሁ መሰል ጀግኖች ደም የፈሰሰባቸው ሸንተረሮች ራቁታቸውን ይታያሉ።

ያ ጎራው ገበየሁ፤ያ ትንታግ ታፈሰ ምን አሉ ምን አሉ

እነ ደጃች ጫጫ፤ እነ ፊታውራሪ ዳመጠው ምን አሉ ምን አሉ

ተማምለው ነበር ከጦሩ ሲገቡ

አልጋውን አቅንተው አድዋ ላይ ቀሩ

እንደሄደ ቀረ እንደገሠገሠ

የንጉሥ ባለሟል ቀኛዝማች ታፈሰ። ተብሎላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) “ታሪክን ለሚመረምር ትውልድ ዓድዋ ውስጥ ህልውናን አፅንቶ የመኖር፣ ዓድዋ ውስጥ ዲፕሎማሲ፣ ዓድዋ ውስጥ ወታደራዊ ስትራቴጂ፣ ታላቅ ውስጣዊ የሕዝቦች ኅብረትና አንድነት፣ ጥበብና ተግባቦት፣ ፍቅርና መስጠት፣ ክብርና ጀግንነት ሞልቶና ሰፍቶ የነበረ መሆኑን እናያለን” ብለዋል። ስፍራዎቹ ግን የደደሆ ቁጥቋጦ እንጂ መታሰቢያ አልባ ናቸው። ስፍራዎቹን ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማልማት በፌዴራልና በትግራይ ክልል መንግስት ትብብር ፕሮጀክቶች መቀረጻቸውም አንድ ተስፋ ነው። የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲም ሌላው ተስፋ ነው። ጉዳዩ ግን “በአድዋ ታሪክ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል ወይ” የሚለው ነው። ዳግማዊ ምኒልክንና እቴጌ ጣይቱን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በጥበብ መርተው ድል በነሱበት ገናና ታሪክ ‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’ እንዲሉ በዘመኑ በህይወት ያልነበሩ ግለሰቦችን ምስል ይዞ (የንጉሰ ነገስቱና ጀግኖች ስም መጥራት እንደ ነውር ቆጥሮ) የሚያከብር ወጣት ትውልድ መግባባት የተሳነው መሆኑን መንገር አያስፈልግም። ዝክረ አድዋ ከአንድነትና መተባበር ይልቅ መነታረኪያ በዓል ከሆነ በርግጥም መግባባት ማጣት ብቻ ሳይሆን የአባቶችን ውለታ መካድ፣ አደራ ሰልቃጭነት ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ‘የዓድዋ ድልን ከሥነ ጥበብ፣ ከእምነት፣ ከፍልስፍና፣ ከታሪክ፣ ከሴቶች ተሳትፎ፣ ከመሪነት ጥበብ፣ ከአገራዊ አንድነት፣ ከውትድርና ሳይንስ፣ በኢኮኖሚ ራስን ከመቻል፣ ብሎም ከጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግልና የታሪክ ፋና ወጊነት ጋር በማስተሳሰር ዓለም አቀፋዊ ሥራ ማከናወን’ የሚቻለው መግባባት ሲኖር ብቻ ነው። በአድዋ ተራሮች ግርጌ ቆሞ ትናንትና ዛሬን ለመዘነ፣ በጽሞና ላሰላሰለ በራሱ ትውልድ አድራጎት አንገቱን በኩራት ቀና ማድረግ ሳይሆን በሐፍረት ሊደፋ ይችላል። እንድንግባባ ደግሞ የተዛባ ትርክትን ማረም፣ ትውልድን ማነጽ ያሻል።

ከ’ሸዋ እስከ አድዋ’ ታሪካዊ ስፍራዎች መታሰቢያ ይፈልጋሉ።