የላሊበላ አብያተ ክስቲያናት ጥገና በፍጥነት ገቢራዊ እንዲሆን መንግስት በጀመረው ትኩረት ልክ እንዲንቀሳቀስ ተጠየቀ

467

ላሊበላ መጋቢት 6/2011 የላሊበላ አብያተ ክስቲያናት ጥገና በፍጥነት ገቢራዊ እንዲሆን መንግስት በጀመረው ትኩረት ልክ አንዲንቀሳቀስ የላሊበላ ከተማ የሃይማኖት አባቶችና ነዎሪዎች ጥሪ አቀረቡ።

የአካባቢው ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች መንግስት ቅርሱን ለማስጠገን የሰጠውን ትኩረትና በአጭር ጊዜ  ያከናወናቸውን ተግባራት አድንቀዋል።

በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከወጥ አለት ተፈልፍለው የታነጹት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በቁጥር 11 ሲሆኑ፤ አብዛኛዎቹ  የድረሱልኝ ጥሪ በሚያሰማ ገጽታ ላይ ይገኛሉ።

አብያተ ክርስቲያናቱ ከኖሩበት ረዥም እድሜ በተጨማሪ ቅርሶቹን ለመጠገን ከንግስት ዘውዲቱ ጀምሮ የተደረጉ ሙከራዎች በጊዜ ብዛት በቅርሱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ይነገራል።

በተለይ ከ10 ዓመት በፊት ጀምሮ በቅርሶቹ ላይ የተቀመጡት የጣሪያ ከለላዎች ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳባቸው ቆይቷል።

የቅርሱን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረስ ተከትሎም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስፍራው ድረስ በማቅናት ጉዳቱን የተመለከቱ ሲሆን፤ በጥቂት ጊዜያት ልዩነት ከፈረንሳይ መንግስት ለቅርሱ ጥገና የሚሆን ፈንድ ማግኘታቸውን ማብሰራቸው ይታወሳል።

በያዝነው ሳምንትም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አብያተ ክርስቲያናቱን ከጎበኙ በኋላ ፈረንሳይና ኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረም ችለዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የላሊበላ ከተማ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች መንግስት ፈንድ ለማፈላለግ የሰጠውን ትኩረት  አድንቀው፤ ጥገናውን በቶሎ ለማስጀመር መሰል ተግባር እንዲፈጸም ጥሪ አቅርበዋል።

መጋቢ ሰጠ መላኩ ” መንግስት እራሱ በቅድሚያ ይሄን ብረት ተነስቶ በአስቸኳይ ጥገና ተደርጎ ህልውናው፤ ለዓለም መኩሪያ፤የኢትዮጵያውያን መኩሪያ  እንዲሆን ጥሪ አቀርበዋል”

ፍቅርና ሰላም ሲኖር፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተስማምቶ በቶሎ ግንባታውን ማስጀመር ይገባል ያሉት  መጋቢ አዕላፍ ሰመረ ናቸው ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ አስተዳደር መምህርና የላሊበላ ቅርስ ጥገና አጥኚ ቡድን አባል የሆኑት ዶክተር መንግስቱ ጎበዜ በበኩላቸው ከአካባቢው የአየር ጠባይ አንጻር በአብያተ ክርስቲያናቱ የተገነባው መጠለያ ጉዳት ሊያደርስ አንደሚችል በጥናት መረጋገጡን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያውያን ፈረንሳዊያን ባለሙያዎች የቅርሱን ጥገና በሚመለከት ጥናት ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ በጥናቱ እስካሁን የተሰሩ የጥገና ስራዎች ለምን ውጤታማ አልሆኑም የሚለው ተለይቷል ነው ያሉት።

ይህም ውጤታማ የሆነ የጥገና ስራዎች በቀላሉ ለማከናወን አንደሚያስችል በመጠቆም።

የላሊበላ ቤተ ጎለጎታ-ቤተ ሚካኤል የጥገና ፕሮጀክት ጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም የወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያምና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬነር በተገኙበት በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

ለጥገና ስራውም የአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ 580 ሺህ እንዲሁም የዓለም ቅርስ ፈንድ 150 ሺ ዶላር መለገሳቸው በወቅቱ ተገልጿል።