የአውሮፕላን አደጋ ምርመራው የአገሪቷን ሉአላዊነት ባስጠበቀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የአቬሽን ባለስልጣን ገለጸ

96

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 ላይ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የደረሰው አደጋ ምርመራ የአገሪቷን ሉዓላዊነት ባስጠበቀ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።

 በምርመራው ሂደት ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ሚና እንዲሁም የአደጋውን ቅድመና ድህረ ሁኔታ አስመልክቶ ባለስልጣኑ ለኢዜአ ገለፃ አድርጓል።

የባለስልጣኑ የኤር ናቪጌሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ክብረአብ በዚሁ ጊዜ እንዳሉትም የአውሮፕላኑን የአደጋ መንስኤ የማጣራት ሂደት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ባስጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ነው።

ባለፈው እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ይበር የነበረ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በመከስከሱ 157 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

አደጋው ከደረሰ ከሁለት ቀናት በኋላ የተገኘውና ለምርመራ ወደ ፈረንሳይ የተላከው የመረጃ ሳጥን (Black Box) የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ ዋናውን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ ውጤቱ እየተጠበቀ ይገኛል።

በመሆኑም የምርመራ ሂደቱ ዓለም አቀፉን የሲቪል አቬሽን ሕግ ተከትሎ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

አውሮፕላኑ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ከመነሳቱ በፊት ደረጃውን የጠበቀ የቅድመ በረራ ዝግጅት (ሴፍቲ) እንደተደረገለት አስታውሰው በበረራ ላይ እንዳለ ከስድስት ደቂቃ በኋላ መከስከሱን አስታውሰዋል።

ከስድስት ደቂቃ በፊት በነበረው ግንኙነት አብራሪው አውሮፕላኑ ችግር እንደገጠመው ገልፆ ለመመለስ የአየር ተቆጣጣሪዎቹን ፈቃድ በጠየቀበት ደቂቃ ውስጥ የማረፊያ ቦታ፣የእሳት አደጋና የሀኪሞች ቡድን ተዘጋጅቶ በመጠባበቅ ላይ እንደነበሩም አስረድተዋል።

እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለፃ አውሮፕላኑ ከራዳር ከተሰወረ በኋላም በሲቪል አቬሽን ሥር የፈልጎ ማዳን ዳይሬክቶሬት አማካኝነት በተቋቋመው ግብረ ሃይል አውሮፕላኑን ፈልጎ የማዳን ሥራ ተከናውኗል።

በእለቱ በፈልጎ ማዳን ሥራው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሄሊኮፕተሮች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የአቢሲኒያ ንግድ አነስተኛ አውሮፕላኖች ተሳትፈዋል።

በሃኪሞች ቡድንና የጸጥታ ኃይሎች ትብብር ከጥቂት ጊዜ ፍለጋ በኋላም አውሮፕላኑ ተከስክሶ መገኘቱን ገልጸዋል።

እነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች ዓለም አቀፉን የአቬሽን ሕግ ተከትሎ መከናወኑን የገለጹት ዳይሬክቶሩ፤ የተሠሩትና እየተሠሩ ያሉት ሥራዎች ለአደጋው መንስኤ መጣራት ግብዓት ሆነው ያገለግላሉ ብለዋል።

የአደጋውን መንስኤ ፍንጭ ይሰጣል የተባለው ጥቁር ሳጥን ሁለት ቅንጣት ያለው ሲሆን፤ አንዱ ፍላይት ዳታ ሪኮርደር፤ ሁለተኛው ደግሞ ኮክፒት ቮይስ ሪኮደር መሆኑን አስረድተዋል።

እነዚህ ሁለቱ በአደጋ ጊዜም ሆነ በሌላ ተፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ቁልፍ መረጃዎችን ይዘው የሚቆዩና አስፈላጊ ሆነው በሚገኙበት ጊዜም መረጃው ተገልብጦ ጥቅም ላይ ማዋል እንዲቻል ሆነው የተሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሁለቱ ክፍሎች (ቅንጣቶች) የበረራን ጠቅላላ ሁኔታ መዝግበው የሚይዙ ሲሆኑ አውሮፕላኑ ምን ያህል ፓወር ሴቲንግ ላይ እንደነበረ፣የኢንጂኑ ፓራሜትሮች የት ላይ እንደነበሩ ያመላክታሉ።

የአውሮፕላኑ ፍጥነት፣ ከፍታው፣ አቅጣጫው በምን ሁኔታ ላይ እንደነበረ በጠቅላላው ሰፋ ያለ መረጃን አጭቀው የሚይዙ ሲሆን፤ እነዚህን መረጃ መዝጋቢዎች የ25 ሰዓት መረጃን የመመዝገብ አቅም እንዳላቸውም ተገልጿል።

የድምጽ መቅጃው (ቮይስ ሪኮርደር) ደግሞ በጋቢና ውስጥ በረዳት ፓይለቱና በአብራሪው እንዲሁም በሌሎች የአውሮፕላኑ ሠራተኞች መካከል የተደረገን ንግግር ቀድቶ የሚይዝም ነው።

ከበረራ ሠራተኞችም ሆነ ከተሳፋሪዎች መረጃ ማግኘት አዳጋች በሆነባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም ተዛማጅ መረጃ በማይገኝበት ደረጃ ብቸኛው የመረጃ ምንጭ ጥቁር ሳጥን (Black Box) ይሆናል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የአደጋውን ሁኔታ ሊያመላክቱ የሚችሉ በርካታ መረጃዎችን ከዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድኑ ጋር በመሆን እየተዘጋጀ ይገኛል።

ጥቁር ሳጥን በገለልተኛ ሀገር እንዲመረመር ከማድረግ አንስቶ የራሷን ባለሙያዎች በማሳተፍ በአስካሁኑ ሂደት ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን ባስጠበቀ መልኩ እያከናወነች ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ሂደቱ በዚሁ ሁኔታ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

አንዳንድ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሚዲያዎች የምርመራ ሂደቱ ሳይጠናቀቅ በአንድ ወገን አድልቶ ስለ አደጋው ብያኔ ላይ መድረስ ከሕግም ሆነ ከሞራል አንፃር አግባብ አለመሆኑን ተረድተው ውጤቱን በትዕግስት እንዲጠባበቁ አሳስበዋል።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ/ም በበረራ ቁጥር ET- 302 ወደ ኬኒያ ሲመራ የነበረው ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ -8 አውሮፕላን ተከስክሶ 157 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት ከሆነ በኋላ ካምፓኒውን ጨምሮ ከ50 በላይ የሚሆኑ የዓለም ሀገራት አውሮፕላኑን ከበረራ ማገዳቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም