የተሽከርካሪ አደጋን ለመግታት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

362

አዳማ መጋቢት  6/2011 የተሽከርካሪ  አደጋን ለመግታትና   የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

የተሽከርካሪን አደጋን  ለመከላከል በማስተማርና ግንዛቤ በማስጨበጥ  በኩል ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር በትብብር መስራት  በሚቻልበት ዙሪያ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ  ተካሄዷል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ በመድረኩ እንዳሉት መስሪያ ቤታቸው አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የተሽከርካሪን አደጋን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው።

ህብረተሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤና ትምህርት እንዲያገኝ ከማስቻል አንፃር የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  ሚና የላቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

የትራፊክ ደህንንት ጉዳይ ራሱን ችሎ በሀገሪቱ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ ከትምህርት ሚንስቴር ጋር እየሰራን ነው” ብለዋል።

የመንገድ ደህንነት የትምህርት ፕሮግራም በመቅረፅ ከ1ሺህ በላይ በሚሆኑ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በፕላዝማ ቴሌቭዥን ለተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚግኝ አመልክተዋል።

በተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርትም  ይሄው  ፕሮግራም እንዲካተት በማድረግ ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ለመድረስና የተሽከርካሪ አደጋን ለመግታት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋልl።

በሌላ በኩል የተሽከርካሪ አደጋ ሲከሰት ተጎጂዎች  የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ በወቅቱ ስለማያገኙ ህይወት ማለፍና ከባድ የአካል ጉዳት እየተዳረጉ ነው፡፡

ለዚህም   በሀገሪቱ  ገጠራማና ከተማ አካባቢዎች የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጋር እየተሰራ መሆኑንም  አቶ ምትኩ አስረድተዋል።

ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት የአሽከርካሪዎች ማስልጠጫ ተቋማትና የብቃት ማረጋገጫ  ማዕከላት ደረጃ የማውጣት ሥራ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ጋርም እንዲሁ፡፡

በሀገሪቱ እየደሰረሰ ያለው የተሽከርካሪ አደጋ አሳሳቢ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በመድረኩ  ጽሁፍ ያቀረቡት በባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ለማ ናቸው፡፡

ከ90 በመቶ በላይ የሚደርሰው የተሽከርካሪ አደጋ  የአሽከርካሪዎች ስነ ባህሪና የሙያዊ ስነ ምግባር ጉድለት መሆኑን የተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት ባለፉት ዓምስት  ዓመታት በሰው ህይወትና ንብረት  ላይ በደረሰው ከ215 ሺህ  በላይ አደጋዎች ውስጥ 150ሺህ የሚሆነው በአሽከርካሪዎች ስህተት ነው፡፡

በዚህም ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት  መውደሙን አመልክተው  በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት መጥፋት፣ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን  ጠቅሰዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 271 የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ላይ ከፁሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ፍቃድ መንጠቅ እርምጃ መወሰዱንም ጠቁመዋል።

“በዋናነት እርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት የሚሰጡት ስልጠና ከደረጃ በታች ከመሆኑም ባለፈ የቴኪኒክ ችግር ያለባቸውና ያረጁ፣ ከትራንስፖር እንቅስቃሴ ውጪ የሆኑ  ተሽከርካሪዎችን ለስልጠናው በመጠቀማቸው ነው “ብለዋል።

እየሰጡ ያሉት ስልጠና አብዘኛው ከተግባር ይልቅ በንድፈሃሳብ ላይ ያተኮረ መሆኑን በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር እንደተደረሰበት አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ተማሪዎች፣ጎልማሶች፣የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች፣የክልልና የፌዴራል የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና የማህበረሰብ ሬድዮ ጭምር  መረባረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የትራንስፖርት ባለስልጣን  ከመጋቢት 5/2011ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው  የምክክር መድረክ ከፌዴራልና ከየክልሉ የተወጣጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  ተሳትፈዋል፡፡