56 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ በህዝብ ነጻ የጉልበት ተሳትፎ ተገነባ

554

ነገሌ መጋቢት 6/2011 በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ በህዝብ ነጻ የጉልበት ተሳትፎ 56 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን የወረዳው መንገዶች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቦጋለ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት በተካሄደው የመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ 18 ሺህ ህዝብ ተሳትፏል።

በሕብረተሰቡ ነጻ የጉልበት ተሳትፎ የተሰራው መንገድ 40 ሚሊዮን ብር ግምት እንዳለውም ጠቁመዋል።

አቶ ዮሐንስ እንዳሉት መንገዱ ክረምት ከበጋ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን ሦስት የገጠር ቀበሌዎችን ከወረዳው ማዕከልና ከደቡብ ክልል ጋር አገናኝቷል፡፡

የመንገዱ መገንባት ህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ ስለሚያደርግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በወረዳው በመንገድ ሥራው ላይ ከተሳተፉት መካከል አርብቶ አደር ገለቢቶ ዳንዴ በአካባቢያቸው የነበረው የመንገድ ችግር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ መቆየቱን ተናግረዋል።

“በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ተሽከርካሪ ስለማይገባ ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላኛው ቀበሌና ከተማ ለመሄድ ብዙ ኪሎ ሜትር በእግር ለመጓዝ እንገደድ ነበር” ብለዋል።

ካለፈው ወር ወዲህ መንገዱ ተሰርቶ ለትራፊክ ክፍት በመሆኑ እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች የትራንስፖርት ተጠቃሚ መሆኑን እንደጀመሩ ተናግረዋል።

አቶ ተልተሎ ኮቶላ የተባሉ ሌላው የወረዳው ነዋሪ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በመንገድ እጦት የአምቡላንስ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻሉ በአካባቢያቸው የሦስት ነፍሰ ጡር ሴቶች ሕይወት ማለፉን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመንገዱ መሰራት ወላድ እናቶችን ፈጥኖ ወደጤና ተቋም ለማድረስ ከማስቻሉ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።