ለተፈናቃይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

497

ጎንደር  መጋቢት 6/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመጠለያዎች ሆነው ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች ሩብ ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ፡፡

ለተማሪዎቹ ድጋፉን ያደረገው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ነው።

የቢሮው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቢያዝን ትላንት ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ቢሮው ድጋፉን ያደረገው ተፈናቃይ ተማሪዎቹ በቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ነው።

ለተማሪዎቹ ከተሰጡት የትምህርት ቁሳቁሶች መካከል 28 ሺህ 363 ደብተሮችና ከ13 ሺህ በላይ እርሳስና እስክሪቢቶዎች ይገኙበታል፡፡

ቢሮው ከማዕከላዊ ጎንደር በተጨማሪ በሰሜን ወሎ ቆቦ፣ በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላምና በቻግኒ ዞኖች ለሚገኙ ተፈናቃይ ተማሪዎች ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የትምህርት ቁሳቁሶቹ በአይምባና በትክል ድንጋይ ጊዚያዊ መጠለያዎች ሆነው ለሚማሩ ከ1 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች እንደሚሰራጩ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ተወካይ አቶ ናትናኤል ቢምረው ናቸው፡፡

” በዞኑ በግጭት ሳቢያ 113 ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው 50 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተለይተዋል ” ብለዋል።

በተመሳሳይ ሀይንኒከን ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በጭልጋና በአይምባ ጊዜያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ግምቱ 300ሺህ ብር የሆነ 154 ኩንታል የዳቦ ዱቄት በድጋፍ አስረክቧል፡፡