ጉዞ ከሸዋ-አድዋ (ክፍል ፩)

625

አየለ ያረጋል /ኢዜአ /

ርግጥ ነው-ጊዜ ይዳኛል። ቀደምቶች ይቀደማሉ፤ ኋለኞች ይመራሉ። ስመ ገናና ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤ ጠፍ ስፍራዎች ይከተማሉ። አንጎለላ ለዚህ ምስክር ናት። የዛሬን አያድርገውና አንጎለላ ግዙፍ ከተማ ነበረች። በአንጎለላ ቀዝቃዛ ነፋስ ይነፍሳል፤ የጉብታ ቁጥቋጦዎችን በመራኛ ጭፈራ ስልት እያወዛወዘ። ሰዓቱ ረፋድ ነበር፤ ለዘብተኛ ጀንበር ጨረሯን የፈነጠቀችበት። ስፍራው ወለል ያለ ሜዳ ነው። በአራቱም ማዕዘናት ሲመለከቱ የመልክዓ ምድር ሰገነት የለም። እንደ አከንባሎ በተደፋ ሰማይ ስር ሰፌድ መሰል መልክዓ ምድር ከመጫሚያ ስር ተነጥፏል፤ ብጉር የወረሳት ኩይሳ መሰሏ የ’አንጎለላ’ ኮረብታ ላይ ቁብ ብለው ሲታዘቡ።

መዳረሻዬ ሩቅ ነው፤ አድዋ። መነሻዬ ቅርብ ነው፤ ከነገስታቱ ባድማ ሸዋ። “ስፍራው ‘አንጎ’ ለምትባል ሴት ነበር፤ ባለቤቷ ‘ሎላ’ ይባላል። ንጉስ ሣህለሥላሴ ቦታውን ምትክ መሬት ሰጥተው ለቤተ መንግስትነት ከመውሰዳቸው በፊት” ብለውኛል በስፍራው ያገኘኋቸው የዕድሜ ባለጸጋ አዛውንት። አንጎለላ የዕደ ጥበብ ኢንዱስትሪና የዲፕሎማሲ ማዕከል የነበረች፣ የንጉሥ ሣህለሥላሴ ከተማ፤ የሸዋ ነገስታት ባድማ ናት። ለቤተ መንግስትነቷ ቋሚ ምስክሮች ግን አልጠፉም። የሣህለሥላሴ ባለሁለት ፎቅ ህንፃ ፈራርሶ ምድር ቤቱ ብቻ ይገኛል። በአፄ ልብነድንግል አባት በአፄ ናዖድ የተመሰረተች ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያንም በስፍራው ትገኛለች። ”ቤተ ክርስቲያኗ የነገስታት መሳለሚያ ነበረች” ይላሉ የአካባቢው አባቶች። በፀበልተኞች የተከበበችዋ ደብር በአማኞች አጠራር ‘ሠሚነሽ ኪዳነ ምህረት’ ይሏታል። ቤተ ክርስቲያኗ የአድዋና የአምባላጄውን ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁን አጽም በክብር አስቀምጣለች። በቤተ መንግስቱ ፍርስራሾች ሶስት ግዙፍ ዛፎች ይገኛሉ። እነሱም የችሎት ማስቻያ ዛፍ (ቆባ ይባላል በእኔ ትውልድ ቀዬ)፣ ንጉሱ ከግብፅ ለመብረቅ መከላከያ ያስመጡት የኮርች ዛፍ እና በመኳንንቱ ጠጅ እየጠጣ ማደጉ የሚነገርለት ሾላ ዛፍ ናቸው። ‘ሰሜን ሸዋ ዛፉም፣ ሰዉም፣ አፈሩም ታሪክ ነው’ ያሉትን ምሁር ያስታውሳል። የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ትውልድ ስፍራ (እንቁላል ኮሶ) ከአንጎለላ ቤተ መንግስት ፍርስራሽ ቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል። ንጉሠ ነገስቱና የጦሩ ፊታውራሪ (ጎራው ገበየሁ) አንድ ቀን የተወለዱና በልጅነት በጋራ ቦርቀው ያደጉ ሲሆን ምኒልክ ‘ታላቅ የጥቁር ንጉሠ ነገሥት’፤ ፊታውራሪ ገበየሁ ደግሞ ጀግና የጦር መሪ ሆነዋል። ወደ አድዋ ሲዘምቱም ታማኙ ፊታውራሪ “ግንባሬን ከተመታሁ ከትውልድ ስፍራዬ ቅበረኝ፤ ስሸሽ ጀርባየን ተመትቸ ከወደኩ ስጋዬን ለአሞራ ስጠው” ብለው ለንጉሡ ተናዘዙ። ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ ሕዳር 28 ዘንጉን ይዞ አምባላጄ ሲያዋጋ ዋለ። የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም ደግሞ መድፉን ይዞ አድዋ ላይ ተሰለፈ። ከምንድብድ (አድዋ) ጦር ሜዳ መድፈኛው ፎክሮ ጠላት መሃል ገባ። ግንባሩን ተመቶ መስዋዕት ሆነ። ንጉሱም ከሰባት ዓመታት በኋላ ክርስትና ከተነሱባት ደብር አፅሙን በክብር በማስቀመጥ ቃላቸውን ጠበቁ። በአንድ ጀምበር፣ በአንድ ቀን የተወለዱት፣ በአንድ ልብ ተማምነው አኩሪ ገድል የፃፉት ዳግማዊ ምኒልክና ፊታውራሪ ገበየሁ ለዘላለም ተለያዩ። ከአድዋ ጦርነት መልስ ጃንሜዳ ላይ በነበረ ሰልፍ የቀኝ እጃቸው የፊታውራሪ ገበየሁ ፈረስ ሌጣውን ከፊታቸው ሲያልፍ ዳግማዊ ምኒልክ ስቅስቅ ብለው ማልቀሳቸውን ጸሃፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ፅፈዋል። አዝማሪም የሁነቱን ትንግርት በስንኝ ቋጠሮ አዜመ።

‘አድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው

ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ” የተባለላቸው ታላቁ የጥቁር ንጉስ አበሻን ለጠላት እንቁላል ከመገበር ታደጉት። ከሳምንት በፊት ለ123ኛ ጊዜ ዝክረ አድዋ በጀግኖች ትውልድ ስፍራ (አንጎለላ) በድምቀት ሲከበር ጀግኖች በቦረቁበት ስፍራ ፈረሰኞች በጉግስና ሽምጥ ግልቢያ እንዲሁም በአማርኛና ኦሮምኛ ባህላዊ ጭፈራዎች ዘክረዋቸዋል። ከአዲስ አበባ 140 ኪሎ ሜትር፤ ከደብረ ብርሃን 11 ኪሎሜትር ርቀት ወጣ ብላ ከምትገኘው አንጎለላ የራስ ጎበና ዳጪ የትውልድ ስፍራ በቅርብ ይገኛል። የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ተማራማሪ ምሁር (ዶክተር ደረሰ አየናቸው) ከዚህ በፊት ስለአካባቢው የነገሩኝ ነገርም ነበር። “በተለይ በሚገርም ሁኔታ ጥናት ውስጥ ካገኘኋቸው አንዱ የዚህ አካባቢ ሰዎች በጣም ጥቂት የሚባሉ የህብረሰተብ ክፍሎች ከአንድ ቤተሰብ ብቻ እንኳን ከሁለት ሺህ ማርትሬዛ በላይ ለንጉሱ ረድተዋል፤ ለአድዋ ዘመቻ። ወርጂ የሚባሉ ህዝቦች፤ የወርጂ ህዝቦች ከዚህ ሸዋ የሚገኝ የሙስሊም ማህበረሰብ ነው። ስለዚህ በየጠረፉም በየትኛውም ቦታ ያለ ህዝብ ተከባብሮ የነጻነት ዓርማ የሆነ ምሰሶ የሆነ ስፍራ ነው” ነበር ያሉኝ።

ይቺ ታሪካዊ ስፍራ በቱሪዝም መዳረሻነት ሳትለማ ዘመናት ብትሻገርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲና በዞኑ አስተዳድር ትብብር የተጀመሩ ስራዎች አሉ። ከሶስት ዓመታት በፊት ምድረ በዳ ወደነበረችው አንጎለላ ታሪካዊ ስፍራ የሚያደርስ የጠጠር መንገድ በመዘርጋቱ ከተማ መሆን ጀምራለች። በአንጎለላ ቅርብ ስፍራ ላይ የሚገኘው የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክም በቅርቡ ተመርቋል። ምናልባትም ጥንት የጎጆ ኢንዱስትሪ የነበራት አንጎለላ፣ አሁን ደግሞ የዘመናዊ ኢንዱስትሪ ማዕከል መሆን ያማራት ይመስላል። በ’ጊዜ ዳኛው’ አርምሞ ሸዋን በ’አንጎለላ’ ምሳሌ ስመለከታት እንዲህ ገለጽኳት።

የእመት ‘አንጎ’ ርስት፣

የእምዬ ምኒልክ እትብት ቅሪት፣

የመድፉ ገበሬ የገበየሁ እትብት ወአፅመ መሬት፣

ከነገሥታት፤ ምዕመናን ምስካዬ ኅዙናን፣

የአፄ ናዖድ መሰረት፤ ሠሚነሽ/አንጎለላ ኪዳነ ምህረት፣

የሣህለሥላሴ ንጉሠ ሸዋ ባድማ፣

እንቁላል ኮሶ የኃይለመለኮት አውድማ፣

ሸዋ አገረ ነገሥት የታሪክ አምባ፣

ከአንኮበር እስከ ደብረ ኤባ፣

ከሸንኮራ እስከ ይፋት፤

የኃይማኖት ስውር ስፌት፣

ምድረ ሊቃውንት ሸዋ፣ የታሪክ አውራ፣

ትንሳኤሽ ይበሰር እንጅ? እስከመቸ ዝምታ?

አድማስ ዘለል እውነታሽ ይወራ!

በሸዋ በርካታ የአብያተ መንግሥታት ስፍራዎች ይገኛሉ። ስመ ገናናዋ አንኮበር አንዷ ናት።ወደ አንኮበር ልሂድ፤ ከደብረ ብርሃን 42 ኪሎ ሜትር ወደ ምሥራቅ። ታሪክ እንጂ መሰረተ ልማት ከሌላት አንኮበር ለመድረስ ተራራማና ብርዳማ መልክዓ ምድር፣ ለዓመታት ተወርቶ የማይሰራ ኮረኮንች መንገዷን ማቋረጥ ግድ ይላል። አንኮበር ከአንጎለላ አንጻር ስመ ገናና፤ በታሪክ ገጾችም ደምቃ የተጻፈች ቦታ ናት። አስገራሚ ምናልባትም ለጀብደኛ ቱሪስቶች ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የታደለች ስፍራ። አንኮበር አምባ ላይ ተቀምጦ ግራ ቀኝ መመልከት በተፈጥሮ ሐሴት ይሰጣል። አንኮበር መጀመሪያ የተመሰረተችው በ333 ዓ.ም በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን መንግስት መሆኑን አስጎብኝዎች ይነገራሉ። ማዕከላዊ መንግስት ተብሎ የተመሰረተው ግን በ1262 ዓ.ም በአጼ ዓምደጽዮን ዘመነ መንግሥት ነው። በግራኝ አህመድ ጠፍታለች፤ በአምሃ ኢየሱስ እንደገና ታድሳለች፤ የቤተ መንግሥቱ ማረፊያ /አሁን ሎጅ ሆኗል/ የተራራው አምባ ሶስት ጊዜ ተከርክሟል። በአጼ ቴዎድሮስ የሸዋ ዘመቻ በሸዋ መኳንንቶች ተቃጥላለች። በ1929 ዓ.ም በፋሽስት ኢጣሊያን ወረራም ዳግም ተቃጥላለች። የነገስታቱ ቤቶች ፍርስራሽ ነገሮች ቢኖሩም አምባው ላይ በአሁኑ ወቀት በ1994 ዓ.ም የተሰራ አንድ ሎጅ ብቻ ይገኛል። (በአምባው ተረተር ወይም ጎንና ጎን የእንግዳ ማረፊያዎች ተሰርተዋል)። ዳግማዊ ምኒልክ አንኮበር ላይ 20 ዓመታት ኖረዋል። በ1858 ዓ.ም ነሐሴ 12 ቀን አንኮበር መድሃኒአለም ንግሥና ተቀብተዋል። በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በቁርባን ተጋብተዋል። ከዛ በኋላ ነው ወደ እንጦጦ ያቀኑት።

አንኮበር ቤተ መንግስት ብቻ ሳይሆን የግዞት ቦታም ነበረች። ስፍራዋ የጦር ታሪክ ላላቸው የኢትዮጵያ ነገሥታት በርግጥም ተመራጭነቷ ያስደንቃል። ታሪካዊቷ አንኮበር መልክዓ ምድራዊ አቀማምጧ የንግድ ስትራቴጂ ስፍራም ናት። በአዋሽ አርባ አንኮበር መንገድ እየተሰራ ነው። ወደ ደብረ ብርሃን የሚወስደው መንገድም ቢዘገይም ተጀምሯል። የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተ መዘከርም  ተገንብቶ ተጠናቋል። ይሄኔ ምናልባት ከፊት ቀድማ ኋላ ለቀረችው አንኮበር ለቱሪስት መዳረሻነቷ፣ ለዕድገቷ ተስፋ ይኖራት ይሆናል። ጸጋዬ ገብረ መድህን

“አንኮበር የአምሃየስ በር፤

አድማስ ፈጠር ኬላ ሰበር

አንኮበር የአምባ ላይ አገር

 የኮረብታ ዲብ የአድባር ዛፍ

አንኮበር የአለት ላይ አጥናፍ

ስውር ምድር የአድማሳት ጫፍ…” እያለ ያሽሞነሞናት ምናልባትም ‘መልክዓ አንኮበር’ ግርምት ፈጥሮበት ሳይሆን አይቀርም። ባለቅኔው ብቻ ሳይሆን እንደኔ አንጎለላና አንኮበርን ታሪክና የዛሬ ቁመና በተደምሞ የተመለከተ ሰው ስሜቱን እንዲህ በግጥም መጠየቁ አይቀርም።

የመርድ አዝማች አስፋወሰን፤ የአምኃየሱስ ርስት

የሣህለሥላሴ ወምኒልክ ቤተ መንግሥት

አንኮበር ደብረ ጠበብት፤

የቀጣፊዎች ወህኒ ግዞት

ከነጋድራሷ ማዕከል የአልዬ አምባ ጎረቤት

ከፊት ቀድመሽ፤ ምነው ኋላቀረሽ?

ከጥንት ከጥዋቱ አንስቶ ምነው በረደሽ?

የከሰም፣ አሚባራ፣ አዋሽ የአፋር እቶን፤ ሀሩር፣

ምነው አያሞቅሽ አንኮበር?