በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን አገር አቀፍ የጤና ደህንነት ዕቅድ ይፋ ሆነ

72

አዲስ አበባ  መጋቢት 6/2011 በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን አገር አቀፍ የጤና ደህንነት ዕቅድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች በተገኙበት ዛሬ ይፋ ሆነ።  

በዚህ ወቅት እንደተገለጸው፤ አገሪቷ መከላከልን መሰረት ያደረገ ስልት ቀይሳ የምታደርገውን ጥረት በጉልህ ይደግፋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ አለመረጋጋት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች እንዳይጋለጡ አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ነው። 

እአአ ከ2019 እስከ 2023 ለሚተገበረው ዕቅድ 10 ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን ወጪው ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት እንደሚሰባሰብ ለማወቅ ተችሏል።        

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደተናገሩት፤ በዕቅድ ዝግጅቱ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ተሳትፎ አድርገዋል።

ዕቅዱ ችገሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ በመለየት መከላከል፣ ችግሮች ሲከሰቱ ፈጣን ምላሽ መስጠት በኅብረተሰቡ ላይ በህመምና በሞት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ስትራቴጂ ነው።   

ባለፉት ሁለት ዓመታት የጤና ሚኒስቴር ከኀብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን ዕቅዱን ዝግጅት ሲደረግ እንደነበረ ገልጸው አገሪቷ በዘርፉ ምን ክፍተት አለባት? የሚለውን በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።   

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ዕቅዱ ከመዘጋጀቱ በፊት አገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል።    

ዶክተር አሚር እንደሚሉት፤ በጥናቱ መሰረት ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት አደጋ ሲከሰት ፈጣን ምላሽ መስጠት መሆኑ የተለየ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት በሁለቱ ከተማ መስተዳደሮችና በዘጠኙ ክልሎች ማዕከላት ተቋቁሟል። 

ከኬሚካልና ጨረር ጋር በተያያዘ አደጋ ቢያጋጥም ምላሽ ለመስጠት በቂ ዝግጅት እንደሌለ በጥናት የተለየ ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመው በዚህም ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል።  

በዕቅዱ ላይ እንደ ክፍተት የተቀመጡ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት 25 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው እቅዱ በአገሪቷ ተላላፊ በሽታዎችና ወረርሽኝን አስቀድሞ ለመግታት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።     

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አገራዊ የጤና ደህንነት እቅዱ ወቅታዊና አስፈላጊ ነው።

አደጋዎችን ቀድሞ የመከላከል፣ ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ የመቆጣጠርና መልሶ የማገገምና እንዳይደገም የማድረግን አቅምን መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም