በክልሉ በመጪው የመኽር እርሻ ከ124 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

78

ጋምቤላ መጋቢት 6/2011 በጋምቤላ ክልል በመጪው የመኽር እርሻ ከ124 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በ2011/12 የመኽር ምርት ዘመን ከ124 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል።

በምርት ዘመኑ ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ  መታቀዱን አመልክተዋል።

ለማልማት የታቀደው መሬት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ31 ሺህ ሄከታር መሬት ብልጫ እንዳለውም ዶክተር ሎው አስረድተዋል።

"ለመሰብሰብ የታቀደው የምርት መጠን  ከአምናው በ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የታየው የድጋፍና የክትትል ክፍተት በዘንሮው ዓመት እንዳይገም ከወዲሁ የባለሙያ ስምሪት ተካሄዶ የንቅናቄ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ለአርሶ አደሮች፣ ለከፊል አርብቶ አደሮችና ለልማት ጣቢያ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንም ዶክተር ሎው አመልክተዋል።

እስከ መጋቢት 15 ባለው ጊዜ ውስጥ 13 ሺህ 139 ኩንታል የበቆሎ፣ የማሽላ፣ የሩዝ፣ የሰሊጥና የለውዝ ምርጥ ዘር ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከእዚህ በፊት በተለምዶ የክልሉ መሬት ለም ነው በሚል የማዳበሪያ ግብዓት ስራ ላይ ሳይውል መቆየቱን ያስታወሱት ዶክተር ሎው በቅርቡ በተካሄደ ጥናት የክልሉ መሬት ስምንት ዓይነት የማደበሪያ ዓይነቶች እንደሚያስፈልጉት መለየቱን አመልክተዋል።

የተመረጡ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ማዳበሪያን በግብአትነት እንዲጀምሩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በቢሮው የሰብል ልማት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ወለጋ ኡሎክ በበኩላቸው "በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ባለሙያዎችን በማሰማራት ግንዛቤን ከመፍጠር ጀምሮ ዘር የማቅረብ ሥራ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የበጋ የመስኖ ግብርና ልማት ሥራቸውን በማጠናቀቅ ለመኸር እርሻ የማሳ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጋምቤላ ከተማ ዙሪያ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አቡላ ዳንጉር ናቸው።

በበጋው የግብርና ልማት የግብዓትና የሙያ ድጋፍ ማግኘታቸውን የገለጹት አረሶ አደሩ በቀጣይ የሚሰጠው ድጋፍ በተመሳሰይ መልኩ በመኽር እርሻ ተጠናከሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በምርት ዘመኑ በሚካሄደው የመኸር ግብርና ልማት 63 ሺህ የሚጠጉ አርሶና ከፊል አርበቶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም