የኪራይ ተመን ማሻሻያው 95 በመቶ ስኬታማ ነው-የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን

531

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በንግድ/በድርጅት ቤቶች ላይ ያደረገው የኪራይ ተመን ማሻሻያ 95 በመቶ ስኬታማ መሆኑን ገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ የቤት ግንባታ ለማስጀመር የውል ስምምነት ስነ-ስርዓትና በንግድ/በድርጅት ቤቶች ኪራይ ተመን መሻሻያ ማጠቃላያ ሪፖርት ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬው እለት ውይይት አካሂዷል።

በዚህ ጊዜ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ የ43 ዓመታት በንግድ/በድርጅት ቤቶች ኪራይ ተመን አንድም ጊዜ ተመን ማሻሻያ ሳይደረግና በተለያዩ ወቅት ማሻሻያ ለማድረግ ቢሞክርም ሳይሳካ ቆይቷል።

ዘንድሮ የኪራይ ማሻሻያ ተመን ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ ሲነሳ ‘የኪራይ ተመኑ ተጋኗል፣ ንግድ ስለቀዘቀዘ አቅም የለንም፣ የልኬት መዛባት አለ’ የሚሉ ቅሬታዎች ቀርበዋል።

የተነሱትን ቅሬታዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲሁም የቤቶቹን ሕጋዊነት በማረጋገጥ፣ ጤናማ የገበያ ውድድር እንዲጎለብትና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ በተሰራው ቁርጠኛ ስራ ኮርፖሬሽኑ ስኬታማ ሊሆን እንደቻለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ ከደንበኞች ጋር ተቀራርቦ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ሲሆን ጉዳያቸው በልዩ ሁኔታ እየታዩ ያሉ ደንበኞች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

”ከህንፃ ከፍታ፣ ለረዥም ጊዜ ውዝፍ ኖሮባቸው በአዲሱ የኪራይ ተመን መሰረት ውል ለመግባት ጥያቄ ያቀረቡ፣ በተለያየ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ውል ሳይዋዋሉ የቆዩ፣ ከያዙት የንግድ ዘርፍ በተጨማሪ የዘርፍ ጥያቄ ያቀረቡ፣ ከአካባቢ ደረጃና ከባቡር መስመር ዝርጋታ ጋር በተያያዘ ለንግድ አያመችም” በሚል የቀረቡ ጉዳዮች መኖራቸውን አቶ ረሻድ ገልጸዋል።

የጥያቄዎቹን ተገቢነት በመለየትና ትክክለኛነት የማረጋገጥ የውሳኔ ሃሳብ በዝርዝ እየተዘጋጀ ሲሆን በቅርቡ መረጃው ለቦርዱ ቀርቦ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በስሩ የሚያስተዳድራቸው ስድስት ሺህ የንግድ/የድርጅት ቤቶች ያሉት ተቋም ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ ቅይጥ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ በአምስት ሳይቶች ቤቶችን መገንባት የሚያስችለውን የውል ስምምነት በዛሬው እለት አካሄዷል።