የፓርቲዎች የጋራ መግባቢያ ሰነድ ዝግጅት በመነጋገር መግባባት እንደሚቻል ያሳያል -ወይዘሪት ብርቱካን

691

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአሰራር ቃል ኪዳን ሰነድ የዝግጅት ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች የነበራቸው ተሳትፎ በመነጋገር መግባባት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገለጹ።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በሰነዱ የዝግጅት ሂደት በአገሪቷ ያሉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ አድርገዋል።

ፓርቲዎቹ የነበራቸው ተሳትፎም ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት መልካም ጅምር የታየበት ነበር ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመካከላቸው መግባባትና መደማመጥ እንዲሁም በመደራደር የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደረስ ተሞክሮ ያገኙበት አጋጣሚ እንደነበርም ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብር በማድረግ ረገድ ጅምሩ ጥሩ ስኬት የታየበት መሆኑን ያነሱት ወይዘሪት ብርቱካን በቀጣይም ይሄው ተግባር ሊለመድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ ተስማምተውበት ትናንት የተፈረመው የጋራ ቃል ኪዳን ሰነድ ለማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አሳታፊና የአሰራር ተገዢነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሰላም በማክበርና ግጭትን በማስወገድ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ከዚህ አንፃር በፓርቲዎቹ የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ ታሪካዊና ልዩ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሂልተን ሆቴል ይፋ የተደረገውን የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ 107 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈርመዋል።