ኮርፖሬሽኑ በመዲናዋ በ5 ሳይቶች ቤቶችን መገንባት የሚያስችለውን የውል ስምምነት ወሰደ

174

አዲስ አበባ መጋቢት 6/72011 የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ ቅይጥ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ በአምስት ሳይቶች ቤቶችን መገንባት የሚያስችለውን የውል ስምምነት ወሰደ ።


ተቀዳሚ ተግባሩ ቤት ገንብቶ ማቅረብ መሆን እንዳለበትም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

ኮርፖሬሽኑ የቤት ግንባታ ለማስጀመር የውል ስምምነት ስነ-ስርዓትና በንግድ/በድርጅት ቤቶች ኪራይ ተመን መሻሻያ ማጠቃለያ ሪፖርት ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬው እለት ውይይት አካሂዷል።

ቤቶቹ በሁለት ምዕራፍ የሚገነቡ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተዘጋጀው 18 ሄክታር መሬት ውስጥ ለመጀመሪያው ዙር 1 ነጥብ 9 ሄክታር የቦታ ዝግጅት ሲጠናቀቅ በድሬዳዋ ደግሞ አራት ሄክታር መሬት ተለይቶ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በአዲስ አበባ የሚገነቡት ቤቶች በአምስት ሳይቶች በ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ሲሆን ቤቶቹ የሚገነቡት በገነተ-ኢየሱስ፣ በመካኒሳ፣ በብሪታኒያ ኤምባሲ፣ በአዋሬና በቦሌ አካበቢዎች ነው።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል እንደገለጹት፤ የቤቶቹን ግንባታ ለማስጀመር የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ የሰው ኃይል ማሟላት፣ ቦታዎችን ለይቶ በይዞታዎቹ ላይ የቅየሳ፣ የአፈር ምርመራ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት የማሟላት፣ የዲዛይን፣ የስታንዳርድና የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ይገኛል።

ህግና ስርዓትን ተከትሎ ጨረታ የማውጣትና በዛሬው እለት የውል ስምምነት የማድረግ ተግባርም የዝግጅቶቹ አካል መሆናቸውን አክለዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ ዣንጥራር አባይ በበኩላቸው መንግስት የቤት ችግርን ለመፍታት ስትራቴጂ ቀርጾ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ስኬት ቢያስመዘግብም የህዝቡን ፍላጎትና አቅርቦት ማጣጣም እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

በተለይም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ እንዲሁም በክልል ዋና ዋና ከተሞች የሚታየው የቤት ፍላጎት ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው ኮርፖሬሽኑ ቤት እየገነባ እንዲያቀርብ የሚያከናውናቸው ተግባራት ተቋማዊ ሆነው መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ኮርፖሬሽኑ የራሱ ገቢ የሌለው፣ ዓመታዊ በጀት ከመንግስት የማይመደብለትና ያለውን ውስን ሃብት የሚመነጨው ከሚከራዩ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ብቻ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ብዙ ቤቶችን መገንባት እንዳላስቻለው ገልጸዋል።

በአንድ በኩል የቤት ጥያቄን ለመመለስ ቤት መገንባት በሌላ በኩል የቤት ግንባታ ለማከናወን የፋይናንስ ችግር ፈታኝ በሆነበት ሁኔታ ሁለቱንም እያጣጠሙ በብልህነት መምራት ተገቢ እንደሆነም አመልክተዋል።

የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳ ኮርፖሬሽኑ የቤቶች ኪራይ ተመን ማሻሻያ በማድረግና የራሱ ገቢ በማመንጨት ቤቶች ገንብቶ የቤት ችግርን ለመፍታት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ጠቁመዋል።

''ኮፖሬሽኑ በቅርቡ ያደረገው የቤት ተመን ማሻሻያ ስራዎች 95 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ቤቶቹን ገንብቶ የህዝቡን ችግር ለመፍታት የኮርፖሬሽኑ ደንበኞችና የሚመለከታቸው አካላት ተናበው መስራት ይገባቸዋል'' ብለዋል።

ቤቶቹ ከኪራይ ከሚገኝ ገቢና ከባንክ በሚገኝ የፋይናንስ ምንጭ የሚገነባ ሲሆን የሚገነቡት ቤቶች ከሰባት እስከ 10 ወለል የሚደርሱና ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም