ክልል አቀፍ የቼዝ ውድድር በመቀሌ ከተማ ተጀመረ

63

መቀሌ መጋቢት 6/2011 በትግራይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የቼዝ ውድድር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀመረ፡፡

በውድድሩ በአገር አቀፍ ደረጃ  ከሚያዝያ 5 እስከ 16 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ለሚካሄደው የክለቦችና የግል ሻምፒዮና ውድድር ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞች እንደሚመረጡ ተነግሯል ።

የትግራይ ክልል ቼዝ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ካህሳይ ፍሰሃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በክልሉ ከዚህ ቀደም የቼዝ ስፖርት ትኩረት የተሰጠው አልነበረም ።

ውድድሩም ከግል ደረጃ ያለፈ ባለመሆኑ የዘርፉ ስፖርት ሳያድግ መቆየቱን ጠቁመዋል ።

"ዘንድሮ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በክልል ደረጃ 12 ክለቦች ተደራጅተው ውድድሩ ተጀምሯል" ብለዋል ።

ከክለቦቹ መካከል አራቱ የሴቶች መሆናቸውን የገለፁት ባለሙያው በግልና በክለቦች መካከል ለአራት ቀን በሚካሄደው ውድድር 100 ስፖርተኞች ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በውድድሩ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ለሚያጠናቅቁ አሸናፊዎች የሜዳሊያ፣ የዋንጫና የገንዘብ ሽልማት ይበረከታል።

ከተወዳዳሪዎች መካከል ወጣት ያሬድ ኃላፎም በሰጠው አስተያየት " ስፖርቱ በመንግስትና በስፖርት ማህበረሰቡ ትኩረት ከተሰጠው በክልልና በሀገር ደረጃ የሚወከሉ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት ይቻላል" ብለዋል።

ወጣት ሳምራዊት ተክሉ በበኩሏ "ቼዝ የአካል ጥንካሬን ሳይሆን የአዕምሮ ብቃት የሚጠይቅ የስፖርት አይነት ነው" ብላለች፡፡

ለስፖርት አይነቱ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ወጧቷ አመልክታለች ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም