የአምቡላንስ አገልግሎት በወሊድ ወቅት ሲደርስብን የነበረውን እንግልት አስቀርቶልናል….በባሌ ዞን አርብቶ አደሮች

493

ጎባ መጋቢት6/2011 የአምቡላንስ አገልግሎት በአቅራቢያቸው ማግኘታቸው በወሊድ ወቅት ሲደርስባቸው የነበረን እንግልት እንዳስቀረላቸው በባሌ ዞን የመዳ ወላቡ ወረዳ ሴት አርብቶ አደሮች ገለጹ፡፡
የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት በበኩሉ የአምቡላንስ አገልግሎት በየወረዳው ተደራሽ መሆንና በጤና ተቋማት የተገነቡ የእናቶች ማቆያ ማዕከላት በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር እንዲጨምር ማገዙን ገለጿል፡፡
ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሙኒራ ከማል ለኢዜአ እንዳሉት ከዚህ በፊት የአምቡላንስ አገልግሎት በአካባቢያቸው በለመኖሩ የመጀመሪያ ልጃቸውን በልምድ አዋለጅ በቤት ውስጥ ለመውለድ ተገደዋል።
በወቅቱ ባጋጠማቸው ረጅም ምጥ ምክንያት በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው መውለዳቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ሙኒራ “በእዚህም ጤናዬ ታውኮ ነበር” ብለዋል።
በአካባቢያቸው አምቡላንስ በመመደቡና ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ሁለተኛ ልጃቸውን በጤና ጣቢያ ካለምንም ችግር በሰላም መውለዳቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮዋ እንዳሉት በጤና ተቋማት የሕክምና አገልገሎት አሰጣጥ መሻሻልና የአምቡላንስ አገልግሎት ተደራሽ መሆን እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ፍላጎታቸውን አሳድጎታል፡፡
ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ሀምዚያ አብደላ በበኩላቸው “ከዚህ በፊት ወላድ እናቶች ፈጥነው ወደ ጤና ተቋማት ባለመድረሳቸው ሕይወታቸው በመንገድ ላይ ያልፍ ነበር” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግስት የአምቡላንስ አገልግሎት በአካባቢያቸው ተደራሽ በማድረጉ እናቶች በጤና ተቋማት በባለሙያ እገዛ እየወለዱ መሆኑንና ይህም ይደርስባቸው ከነበረው የጤና እክል እንደታደጋቸው ተናግረዋል፡፡
በጤና ጣቢያዎች የተገነቡ የእናቶች ማቆያ ማዕከላት ለወሊድ ሁለት ሳምንት የቀራቸው እናቶች እስኪወልዱ ድረስ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ከበዳ ናቸው፡፡
የባሌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ቶሎሳ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 20 ሺህ የሚሆኑ እናቶች በጤና ተቋማት ወልደዋል፡፡
በጤና ተቋማት ከወለዱ እናቶች መካከል 45 በመቶ የሚሆኑት የአምቡላንስ አገልገሎት ተጠቅመው ወደ ሕክምና ተቋም የመጡ ናቸው፡፡
“በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተገዙ 62 አምቡላንሶች ለከተማና ለገጠሩ ህብረተሰብ በቅርበት አገልግሎት መስጠታቸው በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲጨምር የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው” ሲሉም ገልጸዋል ።
የአምቡላንሶች ተደራሽ መሆን በተለይ በገጠሩ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት ነፍሰ ጡር ሴቶችንና ህሙማንን በቃሬዛ ወደ ጤና ተቋም ይወስድ የነበረው ሁኔታ አስቀርቷል።
በተለያዩ ጤና ተቋማት 90 የእናቶች ማቆያ መዕከላት ተሰርተው የምግብና የመኝታ አገልግሎት መስጠታቸው ለነፍሰ ጡር እናቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።
በዞኑ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በየደረጃው በሚገኙ ጤና ተቋማት 70 ሺህ ለሚሆኑ እናቶች የቅድመና የድህረ ወሊድ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ታውቋ።
—END—