በአዲስ አበባ 10 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት ሊጀምሩ ነው

96

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 በ10 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ህክምና የማወለድ አገልግሎት ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ዘመንፈስ ቅዱስ እንደገለጹት፤ በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት ፍላጎትን ለማሟላት በተያዘው ዓመት 10 ጤና ጣቢያዎች ላይ ለመጀመር እየተሰራ ነው።

የቀዶ ህክምና አገልግሎቱ የማዋለድ ምጣኔያቸው ብዙ በሆኑ፣ በተመረጡና ከሆስፒታሎች ርቀት ላይ ባሉ ጤና ጣቢያዎች ይሰጣልም ብለዋል።

እስካሁን አምስት ጤና ጣቢያዎች የማዋለድ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በቀጣይም በአስር ጤና ጣቢያዎች ላይ አምጠው መውለድ ለማይችሉ እናቶች የአገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል።

ስራው የሚከናወነው ከተለያዩ ሆስፒታሎች ጋር ትስስር በመፍጠርና የባለሙያ ዝውውሮችን በማካሄድ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱ ከሚሰጥባቸው አካባቢዎች ተሞክሮ መቀሰሙን ገልጸዋል።

አገልግሎቱን ለመጀመር የባለሙያ እጥረት፣ የቁሳቁስና የበጀት ችግሮች የተለዩ ሲሆን ይህንን ለመፍታት ከሆስፒታሎችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ የእናቶችና የህጻናት ሞት ለመቀነስ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽ ዕቅድን ለማሳካት እንደሚረዳም ተናግረዋል።

በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት የጀመረው የጃንሜዳ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ጋሻው አያሌው፤ ''የቀዶ ህክምና አገልግሎት በጤና ጣቢያ ደረጃ እንዲጀመር መደረጉ እናቶችን ያለእንግልት ለማዋለድ ይረዳል'' ብለዋል።

ጤና ጣቢያው አገልግሎቱን ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ መስጠት የጀመረ ሲሆን በዚህም ወደ ሆስፒታሎች የሚሄዱ እናቶችን ቁጥር በመቀነስ እናቶች ክትትል ባደረጉበት ተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

አገልግሎቱን ለማዳረስ በጤና ጣቢያዎች የተለያዩ የግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በ10 ጤና ጣቢያ ለሚጀመረው የቀዶ ህክምና የተቋማት መረጣና ቁሳቁስ የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ስራውን ለማስጀመር የሚያስችል ስራ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም