በየካቲት ወር 17 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ

788

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 የገቢዎች ሚኒስቴር በየካቲት ወር 2011  ብቻ 17 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

ገቢው በወሩ ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው 19 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ90 በመቶ አፈፃፀም ያለው ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በአንድ ወር ከሚሰበሰበው ገቢ ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ እንደገለጹት፤ በየካቲት 2011 ዓ.ም ከፍ ያለ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የተሻለ ገቢ የተገኘበት ነው። ከዚህ በፊት ከ15 ቢሊዮን ብር ያለፈ ገቢ የተሰበሰበበት ወር የለም።

ከተሰበሰበው ገቢ 93 በመቶ የሚሆነው ከአገር ውስጥ የተገኘ ገቢ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የተገኘው ገቢ ህዝቡ ግብር ለመክፈል ያሳየው ድጋፍ “የግብር ንቅናቄው ተጨባጭ ውጤት ነው” ብለዋል።  

እንዲሁም እያሽቆለቆለ መጥቶ የነበረው የጉምሩክ ገቢ በየካቲት ማንሰራራት መታየቱን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው የካቲት ዕዳና ውዝፍ የማስመለስ ስራ ተጠናክሮ የታየበት ወቅት ሲሆን፤ በወሩ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ወይዘሮ አዳነች አስረድተዋል።

በአቤቱታ ለብዙ ዓመታት ተይዘው ከነበሩ መዝገቦች 177ቱ ውሳኔ እንደተሰጠባቸው የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ለወሩ ገቢ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ጠቁመዋል። 

እንደ ወይዘሮ አዳነች ገለጻ ግብር ከፋዩ የተጨማሪ እሴት ታክስ ዜሮ ማሳወቅና ተመላሽ መጠየቅ ሁኔታ በየካቲት 2011 ዓ.ም ቀንሶ የታየበት ከመሆኑም በላይ በርከት ያለ ትርፍ ማሳወቅ መታየቱን ነው ያመለከቱት።

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት 160 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 130 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸው ፤ ከፀጥታ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አኳያ የተሻለ ገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ አሳካዋለሁ ብሎ ካስቀመጠው አጠቃላይ ገቢ አኳያ ሲታይ አሁንም የገቢ አሰባሰቡ ክፍተት እንዳለበት ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።

በተለይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ አሰባሰብ ላይ ያለው ክፍተት አሁንም መቀጠሉን አመልክተዋል።

ከግብር አሰባሰቡ ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ጨምሮ ሚኒስቴሩ በግብር ከፋዩ ላይ የሚታዩት ተግዳሮቶችን ለመፍታት የማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተደጋጋሚ በግብር ከፋዩ ዘንድ ቅሬታ ይነሳባቸው በነበሩ ከ40 በመቶ በላይ በሚሆኑት ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።

ገቢ አሰባሰቡን የተሻለ ለማድረግና ቀድሞ የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ተናግረዋል።