ፍርድ ቤቱ ቋንቋዎችን የሚያስተረጉሙ ባለሙያዎት እጥረት እያጋጠመው ነው

576

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 ለህብረተሰቡ የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት በፍርድ ቤቶች ውስጥ በተለያየ ቋንቋ የሚያስተረጉሙ ባለሙያዎት እጥረት እያጋጠመው መሆኑን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀ 20 ቁጥር 7 ላይ የተከሰሱ ሰዎች የፍርድ ሂደቱ በማይሰሙት ቋንቋ በሚካሄድበት ወቅት በመንግስት ወጪ የተመሰረተባቸውን ክስና ክርክር በሚሰሙት ቋንቋ እንዲተረጎምላቸው የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ተቀምጧል።

የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች በፖሊስ ተከሰው ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጊዜ የተመሰረተባቸውን ክስ በሚያውቁት ቋንቋ እንዲተረጎምላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው።

”ዜጎች በከባድ ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በህግ አዋቂ የመታገዝ ወይም በጠበቃ የመወከል መብታቸው በህገ መንግስቱ የተደነገገ በመሆኑ በሚናገሩት ቋንቋ የሚያስተረጉም አካል ማግኝት ይችላሉ” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር ብሄረሰቦች የሚኖሩባት አገር በመሆኗ በፍርድ ቤቶች የሚስተናገዱ ተከሳሾች የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ስለሆኑ ብዙዎቹን ቋንቋዎች የሚተረጉሙ ባለሙያዎችን ለማግኝት ችግር እንዳለ ወይዘሮ ሌሊሴ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ተከሳሾች በሚናገሩት ቋንቋ የፍርድ ሂደቱንም ሆነ የዳኞችን ትዕዛዝ እንዲሰሙ ለማድረግ ፍርድ ቤቱ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቋንቋውን የሚናገሩ ሰዎችን እያስመጣ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተርጓሚዎች እጥረት ችሎቶች እንደሚስተጓጎሉ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቷ በቀጣይ ፍርድ ቤቱ እያካሄደ ባለው የመዋቅር ማሻሻያ መፍትሄ እንደሚያገኝ ተናግረዋል።

የፍርድ ቤቱ ዋና ሬጅስትራር ወይዘሮ ህይወት ማሙሸት እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤቶች በሚካሄዱ ችሎቶች ውስጥ በአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር የሚመጡ ተከሳሾችን ለማስተናገድ በቋንቋ አስተርጓሚዎች ረገድ ሰፊ ክፍተት አለ።

በአጠቃላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 77 ችሎቶች ያሉ ሲሆን በቀን ቢያንስ እስከ አምስት አስተርጓሚ የሚያስፈልግ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል በፍርድ ቤቱ ውስጥ ቋንቋውን የሚናገሩ ሰዎች በትብብር እንዲያስተረጉሙ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

በተለይ የውጭ አገር ቋንቋ አስተርጓሚዎችን በማግኝት ረገድ ሰፊ ችግር እንዳለ የገለጹት ወይዘሮ ህይወት አብዛኛው ችሎቶች ተደጋጋሚ ቀጠሮ እንዲሰጡ እየተገደዱ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት ተግዳሮት እንደተደቀነበት ተናግረዋል።