በክልሉ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆኑ ልማቱ እንዲጠናከር አድርጓል

522

መቀሌ መጋቢት 6/2011 በትግራይ ክልል በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆኑ ልማቱ በየዓመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረጉን የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በየዓመቱ ለሃያ ቀናት እያካሄ  ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለመሬት ለምነት የሚከፈል የሥራ ግብር አድርገው እንደሚወስዱትም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር የሄይስ ገብረ በትግራይ ምስራቂዊ ዞን በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ የቃል አሚን ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ናቸው፡፡

በክልሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጠቃሚ እያደረጋቸው በመሆኑ ልማቱን እንደ ባህል አድርገው በመውሰድ ለ30 ዓመታት ያህል ሳያቋርጡ ልማቱን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

“እኔን ጨምሮ አርሶ አደሩ በየዓመቱ ልማቱን ሳይሰለች እያከናወነ ያለው በእንስሳት መኖና በግብርና ምርት የተሸለ ጥቅም ስላገኘን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

” ከወላጆቻችን የተረከብነውን የልማት ሥራ ወጣት አርሶ አደሮችም ከእኛ በተሻለ የአሰራር ዘዴ እያስቀጠሉት ነው” በማለትም ገልጸዋል።

” የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ሥራው ከወላጆቻችን በመልካም ተሞክሮነት የተረከብነው ሥራ ነው ” ያለው ደግሞ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ጎይተኦም አብረሀ ነው፡፡

ወጣቱ እንዳለው ልማቱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት በአሁኑ ወቅት ከባለቤቱ ጋር በመሆን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው፡፡

“እኔና ባለቤቴ በቀን አንድ ሜትር ጥልቀትና ሦስት ሜትር ስፋት ያላቸው 12 አነስተኛ የውሃ ማቆሪያ ጉድጓዶችን የመቆፈር ግዴታ አለብን’’ ሲልም ተናግሯል፡፡

የተፈጥሮ ሀብትና ጥበቃ ሥራው ለእንስሳት መኖ በቀላሉ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ በአካባቢው ምህዳር ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጣም ወጣቱ መገንዘቡን ነው የገለጸው፡፡

” የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራውን የሕይወት ዘመናችን ሥራ አድርገን ወስደነዋል” ያሉት ደግሞ  ከዞኑ ጉሎ መከዳ ወረዳ ቅልዓት ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተሞክሮ ለመውሰድ የመጡት አርሶ አደር ዲያቆን ጸጋይ ካሳሁን ናቸው፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት በየዓመቱ የሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የመሬት ለምነትን ለማስቀጠል የሚከፈል ዓመታዊ ግብር ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በተሰሩት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች በአካባቢያቸው ተመናምነው የነበሩ ተደፋት መሬቶች በደን እንዲሸፈኑ ማድረግ ተችሏል፡፡

በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ሚከኤለ ምሩጽ በበኩላቸው ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በዘመቻ እየተከናወነ ባለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተሰታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ህዝቡ ለሃያ ቀናት በሚከናወነው የልማት ሥራ ያለ ምንም ክፍያ በነጻ ጉልበት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በክልሉ 70 ሺህ ሄክታር መሬት በሚሸፍኑ ከ1 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡