ለያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የባንክ ወለድ ተከፍሏል

79

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 እስካሁን ግንባታው ላልተጠናቀቀው ለያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እስከ ጥር 2011 ዓ.ም ድረስ ብቻ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የባንክ ወለድ መክፈሉን የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

መደበኛ ብድሩን ለመክፈልም ከፊታችን ሰኔ ወር ጀምሮ 374 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በየሶስት ወሩ መክፈል ይጠበቅበታል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተባባል ውድነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2004 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ እስከዛሬ ያልተጠናቀቀው የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ አፈፃፀም ከ43 በመቶ አላለፈም።

ከባንክ ለተወሰደው ብድር ወለድና ግንባታውን ሲያከናውነው ለነበረው የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እስካሁን በድምሩ 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተከፈሏል።

ከአጠቃላይ ክፍያው 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብሩ ለሜቴክ ሲከፈል ቀሪው ለባንክ ወለድ የተከፈለ ነው።

እንደ አቶ ተባባል ገለፃ፤ ከፊታችን ሰኔ ወር ጀምሮ ደግሞ ዋናውን ብድር ለመመለስ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ከ374 ሚሊዮን ብር በላይ በየሶስት ወሩ መክፈል ይጠበቅበታል።

በ2004 ዓ.ም ሜቴክ አካሄድኩ ባለው የአዋጭነት ጥናት በወቅቱ የፕሮጀክቱ ባለቤት ከነበረው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኢንተርፕራይዝ በሁለት ዓመታት ለማጠናቀቅ የግንባታ ኮንትራት ስምምነት ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን በታህሳስ 2005 ዓ.ም ተቋቁሞ በ2006 ዓ.ም የፋብሪካውን ባለቤትነት ሲረከብ ግንባታው መጠናቀቅ ቢጠበቅበትም ከ20 በመቶ አይበልጥም ነበር።

የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱን እስከሚረከበው ድረስም ግንባታው የተከናወነው ያለማንም አማካሪ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ ከተረከበው በኋላ ግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አማካሪ ሆኖ ቆይቷል።

ሆኖም የችግሩን አሳሳቢነት የገመገመው መንግስት ፕሮጀክቱ የባሰ ኪሳራ እንዳያስከትል በመስጋት ከሜቴክ ጋር የነበረው የግንባታ ውል ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቋረጥ አድርጓል።

በዚህም ከመስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ ውሉ በመቋረጡ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ከሜቴክ የሰነድ ርክክብ አጠናቆ ወደ ሳይት ርክክብ ማምራቱን የገለጹት አቶ ተባባል ግንባታውን አቅም ባለው አካል አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ጨረታ ለማውጣት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2010 ዓ.ም. የፋብሪካውን የግንባታ ሂደት በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተው ነበር።

በጉብኝታቸውም የፋብሪካው ግንባታ ከመጓተቱ ባለፈ የፋብሪካው የድጋፍ ግንብ 600 ሜትር ያህል መሰንጠቁን፣ የኩሊንግ ታወሩ እየሰመጠ መሆኑንና በአካባቢው ረጅም የመሬት መሰንጠቅ መኖሩን አረጋግጠዋል።

የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ በዓመት 300 ሺህ ቶን ዩሪያ፣ 200 ሺህ ቶን አሞኒያ እንዲሁም ሌሎች ኬሚካሎችን በማምረት በ10 ዓመታት ውስጥ የግንባታ ወጪውን ይሸፍናል ቢባልም እስካሁን ተጨማሪ ወጪ በማስከተል ላይ ነው።

ሜቴክ የማዳበሪያ ፋብሪካውን ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ የመንግስት ፕሮጀክት ግንባታዎችን ለማከናወን ከመንግስት 50 ቢሊዮን ብር የወሰደ ቢሆንም ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት አንዱንም ማጠናቀቅ አልቻለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም