በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 235 የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች ተላለፉ

73

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 235 የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች አነስተኛ ገቢ ላላቸዉ ነዋሪዎችና ለልማት ተነሺዎች ተላለፈዋል።

በህገ-ወጥ በመንገድ የተያዙ ቤቶችን ለችግረኞችና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለማስተላለፍ ህዝቡ ጥቆማ እንዲያደርግ ተጠይቋል።

ክፍለ ከተማው የቀበሌ ቤት እንዲያገኙ ያደረጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ናቸው።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ ይገኛል።

በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሁለት እና ሶስት ቤቶችን የያዙ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመው ይህንን በመፍታት ለችግረኞች የቀበሌ ቤቶቹን የማስተላለፍ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ በተለይ ችግረኛ የሆኑትን ለመርዳትና ተጠቃሚ ለማድረግ ያለአግባብ ቤት የያዙ ሰዎችን በማጋለጥ እንዲተባበር ጠይቀዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ በበኩላቸው፤ የህብረተሰቡን ችግር በመለየት በቤቶች ልማት ዘርፍ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ህገ-ወጥ ተግባር ለመከላከል እየተሰራ ይገኛል።

''በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት በህገ-ወጥ ተይዘው የነበሩ እንዲሁም በየመንደሩ የፈረሱና ተዘግተው የተቀመጡ ቤቶችን አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እየተላለፉ ይገኛሉ'' ብለዋል።

በቀጣይም በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችን በማስለቀቅ እንዲሁም ቀላልና ሙሉ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ቤቶች ጥገና በማድረግ አነስተኛ ገቢ ላላቸውና የልማት ተነሺዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የቤት ባለቤት የሆኑ የህብረሰተብ ክፍሎችም ቤት ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው ከተማ አስተዳደሩ ሁሉንም ህብረተሰብ ባማከለና ፍትሃዊነትን ባረጋገጠ መልኩ ለችግረኛ ዜጎች የመስጠት ተግባሩን እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ መኖሪያ ቤቶችንም ህጋዊ በሆነ አግባብ ለህብረተሰቡ እንዲተላለፉ ጥቆማ በመስጠት ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

በክፍለ ከተማዉ የመኖሪያ ቤቶች ለህብረተሰቡ ሲተላለፉ የአሁኑን ጨምሮ ለ3 ጊዜ ሲሆን በአጠቃላይ 735 ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም