ውድድሩ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን የማጎልበት ዓላማ ሊኖረው ይገባል፡-የአፍሪካ ብስክሌት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት

87

ባህር ዳር መጋቢት 6/2011 14ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና አፍሪካዊ ወንድማማችነትን የማጎልበት ዓላማ ሊኖረው እንደሚገባ የአፍሪካ ብስክሌት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ዋጌ አዝሃ መሀመድ ገለጹ። 

በባህር ዳር ከተማ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ዛሬ ተጀምሯል።

ስፖርቱን አስመልክተው ፕሬዚዳንቱ ትናንት በሰጡት መግለጫ የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ከስፖርታዊ ውድድርነቱ ባሻገር የአህጉሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክር በመሆኑ ተወዳዳሪዎቹ ማሸነፍን ብቻ ትኩረት ማድረግ የለባቸውም።

ኢትዮጵያዊያን ለስፖርት ልዩ ፍቅር እንዳላቸው ጠቁመው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮናን እንድታዘጋጅ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የያላሳለሰ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰዋል።

"ውድድሩን ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ የባህር ዳር ከተማ ህዝብ ለእሳቸውና ከየሀገራቱ ለመጡ የልዑካን ቡድን ላደረገው መልካም የእንግዳ  አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በመክፈቻ ስነ-ስርአቱ ላይ እንደገለጹት ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ  የክልሉ መንግስትና የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል።

"ውድድሩ በባህር ዳር ከተማ መካሄዱ ብስክሌት የእለት ተልት መጓጓዣው የሆነው የባህር ዳር ከተማ ህዝብ ወደ ብስክሌት ስፖርት እንዲያዘነብል አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማሳደር ያግዛል" ብለዋል።

በባህር ዳር ከተማ ውድድሩ እንዲካሄድ ለወሰኑት የአፍሪካና የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አመራሮችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳነት አቶ ወርቁ ገዳ በበኩላቸው ባህር ዳር አቀማመጧ ለብስክሌት ውድድር ምቹ መሆኗና ህዝቡም ለብስክሌት ስፖርት ያለው ፍላጎት ከተማዋ እንድትመረጥ ያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።

ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ የባህር ዳር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪ ከተለያዩ አገራት ለመጡ እህትና ወንድም አፍሪካዊያን በተለመደው የእንግዳ አክባሪ ባህሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያድርግ መልክት አስተላልፈዋል።

ከባህር ዳር መውጫ በተለምዶ "ሰባታሚት" ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ መነሻና መድረሻውን አደርጎ ወደ አዴት መስመር 50 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የደርሶ መልስ የክሮኖ ሜትር የብስክሌት ውድድር ዛሬ ተጀምሯል።

ውድድሩም በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች በግልና በቡድን የተካሄደ ሲሆን የአፍሪካ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና ሌሎችም እንግዶች በቦታው ላይ ተገኝተው ውድድሩን አስጀምረዋል።

በ14ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ከ30 በላይ የአፍሪካ አገራት ይሳተፋሉ ተብሎ  ቢጠበቅም በውደድሩ የተገኙት  ከ13 አገራት እንደማይበልጡ ታውቋል።

በውድድሩ ለመሳተፍ ወደባህር ዳር ከመጡ ሀገራትም ከ100 በላይ ተወዳዳሪዎች መገኘታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም