የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ በሶስት ወር ውስጥ ወደሙሉ ትግበራ ይገባል

562

አዳማ መጋቢት 6/2011 ከፍጥነት ጋር በተያያዘ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እንደሚያስችል የታመነበት የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደሙሉ ትግበራ እንደሚገባ የትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ እንዳስታወቀዉ፤ መሳሪያዉ እስከ መጋቢት 30 ድረስ በሙከራ ደረጃ ላይ ይቆያል።

በባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በላይ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ያስችላሉ ተብለው ከተለዩ መፍትሄዎች መካከል የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ ዋነኛው እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ በተሽከርካሪዎች ላይ መግጠም የትራፊክ አደጋን እያደረሱ ያሉ የንግድ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

መሳሪያው በመጀመሪያ እአአ በ2000 በተመረቱ የንግድ ተሽከርካሪዎች ላይ እንደሚገጠምና በቀጣይ በመንግስትና በቤት ተሽከርካሪዎች እንደሚገጠም ገልፀዋል።

ከፍጥነት መቆጣጠር ባሻገር ተሽርካሪው የት አካባቢ  እንደሚገኝ፣ አሽከርካሪዎች በሰሩት ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ አደጋ ሲደርሰበትና የነዳጅ ፍጆታዉንም ለመቆጣጠር መሳሪያው ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁመዋል።

መሳሪያዉን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ መመሪያ መዘጋጀቱንና መሳሪያውን ከውጭ የሚያሰገቡ ድርጅቶች መለየታቸውን አስታውቀዋል።

ባለሰልጣኑ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉ ሌሎች ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት አቶ ያዕቆብ በጥፋተኛ አሽከርካሪዎች ላይ በየጊዜዉ መረጃ በመያዝ አገር አቀፍ  የመረጃ ቋት እየተዘጋጀ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የጥፋተኛ አሽከርካሪዎችን መረጃ መያዝ በተለያዩ ክልሎች በተናጠል ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል።

በአገሪቱ ከ2005 እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ 215 ሺህ 531 ትራፊክ አደጋ ካደረሱት ውስጥ 149 ሺህ 918 ያህሉ በአሽከርካሪዎች ስህተት መሆናቸዉን የባለስልጣኑ መረጃ አሳይቷል።