የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ቀጣይነት ያለው ሠላምን ለማረጋገጥ በሚያግዙ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው

607

ዲላ መጋቢት 5/2011 የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓልን የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍና ቀጣይነት ያለው ሠላም ለማረጋገጥ በሚያግዙ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ ባለው የብሔሩ ቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም  የተገኙት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተካልኝ ታደሰ እንዳሉት የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል” ዳራሮ”  ህዝቡ ምርት ከሰበሰበ በኋላ የሚያከብረው የምስጋና ፤ የይቅርታና የሠላም በዓል ነው፡፡

” ዳራሮ  መሠረቱ ሰላም ነው ” ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው የዘንድሮው በዓል በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍና ቀጣይነት ያለው ሠላም ለማረጋገጥ በማግዙ ዝግጅቶች  እየተከበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡

በሲምፖዚየሙ እየቀረቡ ያሉ ጥናታዊ ፅሁፎችም የብሔሩን ነባር የሠላም እሴቶችን ለማጠናከርና የተጋረጠባቸውን ችግሮች በመለየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ በሚያስችል መልኩ የተቃኙ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ተካልኝ ገለጻ በዞኑ ከ172 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች ይገኛሉ፤ የዞኑ አስተዳደር 300 ኩንታል ዱቄት ድጋፍና የህክምና አገልግሎት በየመጠለያ ጣቢያዎቹ እያደረሰ ነው፤ ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመነጋገርም የተለያዩ ሰብአዊ ድጋፎች እያቀረቡ ነው ፡፡

የጌዴኦ ዞን ባህል ፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አሰፋ በበኩላቸው  ዞኑ ሠላማዊ ቢሆንም ከአጎራባች አከባቢ ተፈናቅለው  በዞኑ የተጠለሉ ዜጎች በችግር  ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡        

” የፌዴራሉ መንግስት በአካባቢው ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ቃል የገባውን መተግበር ይጠበቅበታል”  ያሉት አቶ ዮሐንስ የዞኑ አስተዳደር እያደረገ ካለው ድጋፍ ባሻገር ” ዳራሮ “ን ምክንያት በማድረግ ሰፊ ንቅናቄ ተፈጥሮ ከአካባቢው ተወላጆችና ወዳጆች ሀብት የማሰባሰብ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ የብሔሩን ቋንቋና ባህል ለማጎልበትና ጠብቆ ለማቆየት የሚያግዙ ተግባራት እንደሚከናወኑ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ በተጨማሪም በዞኑ ባሉ ከ 575 በላይ ባህላዊ ሸንጎዎች አማካይነት በተለይ ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የሠላም እሴቶች ግንባታ ሥራ በስፋት እንደሚሰራ አብራርተዋል ፡፡

በዓሉን ለማክበር ከሀዋሳ እንደመጡ የተናገሩት አቶ አበራ ኪጴ “የብሔሩ ዘመን መለወጫ ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች በድምቀት ሳይከበር ቢቀርም ዘንድሮ ትኩረት አግኝቶ በዚህ መልኩ መከበሩ ቀጣዩ ትውልድ ባህሉን ሳይሸራረፍ እንዲረከብና እንዲያሳድገው አይነተኛ ሚና ይጫወታል “ብለዋል ፡፡

ጌዴኦ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብሮ የመኖር የዳበረ እሴት እንዳለው አመልክተው ህዝቡ እንደቀድሞ ከሁሉም ህዝቦች ጋር በሰላም የሚኖርበትን ሁኔታ ለመፍጠር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮው በዓል  ከወትሮው በተለየ ድምቀት እየተከበረ በመሆን ልዩ ስሜት እንዳሳደረባቸው የገለፁት ከአዲስ አበባ በበዓሉ ለመታደም የመጡት ወይዘሮ ነፃነት አለሙ ናቸው፡፡

“የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ የሁሉም ህብረተሰብ ጉዳይ በመሆኑ በዞንም ሆነ በሀገር ደረጃ ተቻችሎ አብሮ መኖርን ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰራት አለበት” ብለዋል ፡፡

እስከነገ በሚቆየው የጌዴኦ ብሔር ቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም ላይ ለተፈናቀሉ ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ የተከናወነ ሲሆን የባህላዊ ምግብና ቁሳቁሶች አውደ ርዕይም ይኖራል፡፡