በወረታ ከተማ የሚገነባው የደረቅ ወደብና ተርሚናል የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ሥራ ተጀመረ

488

ባህርዳር መጋቢት 5/2011 በደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ከተማ የሚገነባው የደረቅ ወደብና ተርሚናል የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ሥራ የፌዴራልና የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተጀመረ።

ግንባታው በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚገነባ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ግንባታም በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ተጀምሯል።

ግንባታው በአማራ ክልል መንገድ ስራዎች ድርጅት ተቋራጭነት የሚከናወን ሲሆን ሙሉ ወጭው በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖትርና ሎጅስቲክስ አገልግሎት የሚሸፈን ነው።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ይደረግበታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ በደረቅ ወደብና ተርሚናል የመጀመሪያ ዙር ግንባታ የማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተገነቡትና እየተገነቡት ካሉት ስምንት ደረቅ ወደብና ተርሚናሎች አንዱ ነው።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከአራት ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የጠቆሙት ዋና ሥራ አሰፈጻሚው ደረቅ ወደብና ተርሚናሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአንድ ጊዜ 937 ኮንቴነሮችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ግንባታ ሁሉም ምዕራፎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቃ ሀገሪቱ ታወጣ የነበረውን አላስፈላጊ ወጭ እንደሚያስቀር ጠቁመዋል።

ግንባታው በንግዱ ማህበረሰብ በየጊዜው ይነሳ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታም አስረድተዋል።

ደረቅ ወደብና ተርሚናሉ  በተገቢው የጥራት ደረጃና በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደረግም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው “የደረቅ ወደቡ ግንባታ መጀመር ትርፍ አምራች የሆነውን የክልሉን አርሶ አደር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስችላል” ብለዋል።

በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚገነባው ደረቅ ወደብና ተርሚናል አጠቃላይ ግንባታው በ20 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያርፍም ታውቋል።