የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን በትምህርት ስርዓት ውስጥ ለማካተት እየተሰራ ነው

221

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን በትምህርት ስርዓት ውስጥ ለማካተት እየተሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡    

በባለስልጣኑ አዘጋጅነት 'የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚዲያ ተቋማት ሚና' በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀን የሚቆይ ስልጠናና ውይይት በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡                

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዙሪያ ባከናወናቸው ተግባራት ባለፉት ስድስት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ አደጋ ቀንሷል፡፡   

በተጠቀሱት ወራቶች የተመዘገበው የሞቱ አደጋ 2 ሺህ 198 ሲሆን ይህ አሃዝ ከአምናው ተመሳሳይ ስድስት ወራት ጋር ሲነጻጸር በቁጥር በ117 በመቶኛ ደግሞ በ5 ነጥብ 3 ቅናሽ አሳይቷል፡፡  

በቀጣይም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ መገናኛ ብዙሃንን ከመጠቀም በተጨማሪ የመንገድ ትራፊክ ሕጎችን በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ለማካተት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ በማካተት ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉ ተማሪዎች የትራፊክ ህጎችን እንዲያውቁት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

''ይህም ሕግ አስከባሪን ሳይሆን ህግን የሚያከብር ትውልድ ለመፍጠርና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚረዳ ይሆናል'' ብለዋል፡፡

እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻ ትምህርቱን በጎልማሶች ስርአተ ትምህርት ውስጥ አካቶ ለማስተማርም ሞጁል እየተዘጋጀ ነው፡፡ 

ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ውስጥ እንዲካተትም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በከተማና በሀገር አቋራጭ አውቶብሶች ባሉ ስክሪንና ቴሌቪዥኖች ላይም ግንዛቤን የሚያሳድጉ አጫጭር ቪዲዮዎችን ለማሳየት ታቅዷል።  

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የውይይት መድረክ ባለፈው ዓመት የመንገድ ደህንነት ላይ ግንዛቤን ለማሳደግ የተመሰረተው የሚዲያ ፎረም አፈጻጸምና የባለስልጣኑ የስድስት ወራት ዕቅድ ክንውንም ይዳሰሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም