የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

181

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎችን ልማት የማቀናጀትና የማስተባበር ኃላፊነት ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ወደ ሠላም ሚኒስቴር ተላልፏል።

በዚህም መሰረት የሠላም ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲያዘጋጅ የነበረውን የአርብቶ አደር የፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፍ አጠናቆ እንዲያቀረብ መመሪያ ተሰጥቶታል።

የሠላም ሚኒስቴርም የአርብቶ አደር የፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፍ ረቂቅ አዋጅን አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ዛሬ አስታውቋል።

አዋጁም በዋነኝነት የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ የአርብቶ አደር ልማት በመዘርጋት የአርብቶ አደሩን ተሳታፊነት፣ ባለቤትነት እንዲሁም ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተገልጿል።

በዚህም ባህላዊ እውቀቶችን ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰር፣ የአርብቶ አደሩ የእንሰሳት ኃብት፣ የግጦሽ መሬትና ውኃን መሰረት ያደረገ የልማት አቅጣጫ መቀየስንም ያካትታል።

ይህም ደግሞ ከሥነ-ምህዳሩ ጋር የተጣጣመና ከአገርና ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የተሳሰረ የልማት አቅጣጫ እንደሚሆን በመጠቆም።

መረጃን መሰረት ያደረገ የተፈጥሮ ኃብት አጠቃቀም በመዘርጋት የአርብቶ አደሩን ህይወት ማሻሻልና በዘርፉም የግል ባለኃብቱ እንዲገባ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል አዋጁ።   

አርብቶ አደር ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም ልዩ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ አካላትም ትኩረት እንዲሰጣቸው ያደርጋል ነው የተባለው።

በአርብቶ አደር አካባቢ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች አርብቶ አደሩ ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራርም ለመዘረጋት እንደሚያስችል ተጠቁማል።

ጎን ለጎንም የአርብቶ አደሩ እንቅስቃሴ ድንበር ተሻጋሪ ምጣኔ ኃብታዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ከግምት በማስገባት ድንበር ዘለል ሥርዓትን ለመፍጠርም  ያግዛል።

ይህም ደግሞ አካባቢያዊና አህጉራዊ ትብብር በመፍጠር በጋራ ማልማትን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ በአዋጁ ተገልጿል። 

በሚኒስቴሩ የጥናትና ኃብት ክፍፍል ዳይሬክተር ጄነራል ሻንቆ ደለለኝም አዋጁ የመጨረሻ ማሻሻያ ተደርጎበት አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይገኛል ብለዋል።

አዋጁ እስከዚህ ዓመት መጨረሻም ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ያላቸውን እምነት በመጠቆም።    

አዋጁ እስከዚህ ዓመት መጨረሻም ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገኝ በመጠቆም። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም