ምክር ቤቱ የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል አዋጅን አጸደቀ

312

አዲስ አበባ መጋቢት 5/ 2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 27ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ያጸደቀው።

የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማዕከሉን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ለምክር ቤቱ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ በዝርዝር ተወያይቷል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ረቂቅ ሰነዱ አዋጅ ቁጥር 1123/11 ሆኖ እንዲወጣ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንዳሉት፤ የህጉ መጽደቅ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማስፈን፣ የመቻቻል ባህልን ለማጎልበት፤ ግጭቶችን በውይይትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እና አገራዊ እሴቶችን ለማዳበር የጎላ ሚና ይኖረዋል።

የፌዴራሊዝም አስተምህሮና ተደራሽነትን በማስፋት ኅብረተሰቡ ህገ መንግስታዊ መርሆዎችንና እሴቶችን በመገንዘብ መብትና ግዴታውን በአግባቡ እንዲጠቀምም ያስችለዋል ብለዋል።

በየደረጀው የሚገኙ የተቋማት አስተምህሮዎች በአገር ግንባታ ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ እና ብሔራዊ መግባባትን በማጎልበትም ማዕከሉ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

ህገ መንግስታዊ ስርዓት የተላበሰ፣ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ያዳበረ፤ ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር መራመድ የሚችልና በምክንያታዊነትና በውይይት የሚያምን ተሳታፊ ማኅበረሰብ ለመገንባትም ያግዛል ብለዋል።

የማዕከሉ ዋና መስሪያ ቤት አዲስ አበባ ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ቅርንጫፍ ሊከፍት የሚችል፤ ሰራተኞችንም በሲቪል ሰርቪስ ህግና መመሪያ የሚቀጥርና የሚያስተዳድር መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች እና ስምምነቶች ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ጎሚቴዎች መርቷል።

የከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ልኳል።

በኢትዮጵያ እና በህንድ መንግስት መካከል የተደረገ የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት እንዲሁም በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ማዕከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ሽግግር እና ክልላዊ ትስስር ፕሮጀክት የብድር ስምምነት የቀረበውን ረቂቅም መርቷል።

በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገ የብድር ስምምነት እና በኢትዮጵያና በቻይና  ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ መካከል ለመቀሌ ውሃ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡትን ረቂቅ አዋጆችንም መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።