የቃል ኪዳን ሰነዱ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው- የፖለቲካ ፓርቲዎች

702

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሙት የጋራ የቃል ኪዳን ስነድ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት፤ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትና ዛሬ የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጥሩ ጅምር መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ተቀባይነት ያገኘና መግባባት ላይ የተደረሰበት ሰነድ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ የአገሪቷ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገለጻ የቃል ኪዳን ሰነዱ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ ቃል የገቡበት በመሆኑ ወደፊት ትክክለኛ የዴሞክራሲ ስርዓት በኢትዮጵያ ለመገንባት ያስችላል።

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ሰነዱ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ በመሆኑ ፊርማቸውን ያኖሩ ፓርቲዎች በሙሉ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ቀደም ብሎ በሰነዱ ላይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ የሺዋስ፤ ከፊርማ ሥነ ስርዓቱ በኋላ ላለው ተግባራዊነት የሁሉንም ፓርቲዎች የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ስርዓት በለውጥ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ይኸንን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመምራት ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙኃን ለአገርና ህዝብ ቅድሚያ በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባም አቶ የሺዋስ አሳስበዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ግደይ ዘርዓጽዮን እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመደማመጥ ላይ ተመስርተው ዓላማቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ መወዳደር የሚችሉበት አሰራር ተፈጥሯል።

‘በቅንነት ለዓላማ ብቻ መታገል በቀጣይ ከሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይጠበቃልም’ ሲሉ ተናግረዋል።

የዓረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታ በበኩላቸው ዛሬ የተፈረመው የቃልኪዳን ሰነድ በኢትዮጵያ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም ለአገር አንድነትና ለህዝቦች ደህንነት በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

‘በቀጣይም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈረመው ስምምነት መሰረት መንቀሳቀስ ከቻሉ የዴሞክራሲ ስርዓቱን እውን ማድረግ እንደሚቻል እምነት አለኝ’ ብለዋል።

የጋራ የቃል ኪዳን ሰነዱን ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ 107 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈርመዋል።