የድምጽ ብክለትን የተመለከተ አዲስ ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱ ተገለጸ

443

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የድምጽ ብክለት ቁጥጥርን በተመለከተው አዲስ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ።

ደንቡ የመጀመሪያ ረቂቅ ሲሆን በ1995 ዓ.ም የወጣውን የብክለት ቁጥጥር አዋጅ 300/1995 አንቀጽ 20 መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው።

ረቂቁ ከዚህ በፊት ከወጣው ጥቅል የብክለት አዋጅ በተጨማሪ የድምጽ ብክለትን ነጥሎ የሚያይ መሆኑን በኮሚሽኑ የአካባቢ ብክለት ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉብርሃን ታሪኩ ገልጸዋል።

ረቂቅ ደንቡን በተለያዩ ውይይቶች በማዳበር በተያዘው በጀት አመት መጨረሻ የሚኒስትሮች ምክርቤት ካጸደቀው በኋላ ተፈጻሚ መሆን ይጀምራልም ብለዋል።

የድምጽ ብክለት ቀጠናዎችን የመኖሪያ ፣የንግድ ፣የኢንዱስትሪና ቅይጥ በሚል ዘርፍ በመለየት ለእያንዳንዱ የየራሱ መስፈርት ተቀምጦለት የሚጠቀሙት የድምጽ መጠን እንደየቀጠናቸው የሚወሰን ይሆናል።

በኮሚሽኑ የህግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ መሃሪ ወንድማገኝ የቀደመው አዋጅ ጠቅላላ ብክለትን ለመቆጣጠር የወጣ ቢሆንም ድምጽን  ብክለት ነው ብሎ ያለመቀበል ሰፊ ክፍተት እንደነበረውም ጠቁመዋል።

የድምጽ ብክለትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ሂደትም ሰፊ ችግር መኖሩን ገልጸዋል።

የንግድ ቢሮዎች ፈቃድ ሲሰጡም ተጽእኖውን ግምገመው ስለማያደርጉ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር የላላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አዲሱ ረቂቅ ደንብ ተፈጻሚ ሲሆን ክፍተቱን ይሞላል ተብሎ መታሰቡን ጠቅሰው ንግድ ቢሮዎች ፈቃድ ከመስጠታቸው በፊት አካባቢውን በአካል መመልከት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በተጨማሪም ፈቃድ ሳያወጡ የሚሰሩ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ደንቡ ተግባራዊ ሲሆን ሃይማኖታዊና ብሄራዊ ክብረ በአላት በሚካሄዱበት ጊዜ ያለን የድምጽ ብክለት እንደማያካትት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም