በማዕከላዊ ጎንደር ግጭትና የዜጎች መፈናቀልን በማስቀረት አስተማማኝ ሰላም መስፈኑ ተጠቆመ

63

ጎንደር መጋቢት 5/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በህዝቡና በጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ርብርብ ግጭትና የዜጎች መፈናቀልን በማስቀረት አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን መቻሉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ፡፡

ግጭት በመፍጠር ለዜጎች መፈናቀል፣ ሞትና የንብረት ውድመት እጃቸው አለባቸው የተባሉ 39 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉም ታውቋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምአለው በአካባቢው ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በፌደራልና በክልሉ መንግስት የጋራ ጥረት የተወሰደው እርምጃ ውጤት አስገኝቷል፡፡

በተለይም በጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ የተጣለው ክልከላ በአካባቢው በተናጠልና በቡድን ይፈጸም የነበረውን ግጭት በማስቆም ህግና ስርአትን ማስከበር የተቻለበት ሁኔታ ለመፍጠር ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

"የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ከህዝቡ ጋር በመሆን ያከናወኑት የሰላም ውይይትና የእርቅ ሂደቶች የአካባቢውን ሰላም ዳግም ለመመለስና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር አግዟል" ብለዋል፡፡

የሰላም መስፈን በግጭቱ ተስተጓጉሎ የነበረው የጎንደር - መተማና፤ የጎንደር - ሁመራ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀምርና ተቀዛቅዞ የቆየው የከተሞቹ የንግድ እንቅስቃሴ ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም በግጭቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከእለት እርዳታ ጀምሮ የጤናና የመጠለያ አገልግሎት ለመስጠት ማስቻሉን ነው የገለጹት፡፡

ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚያስችል የማስፈጸሚያ ዕቅድ በማዘጋጀት በግጭቱ ቃጠሎ የደረሰባቸውን ከ4ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ዳግም ለመገንባት የሰላሙ ሁኔታ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

በግጭቱ አገልግሎት መስጠት ያቋረጡ የመንግስት ተቋማትን ወደ ሥራ በማስገባት በኩልም በተለይ በምስራቅና በምዕራብ ደንቢያ እንዲሁም በላይ አርማጭሆ ወረዳዎች የትምህርትና የጤና ተቋማትን ዳግም ሥራ ማስጀመር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በግጭቱ ተሳታፊ ናቸው ተብለው በህዝቡና በጸጥታ ኃይሉ የተለዩ ጸረ ሰላም ኃይሎችን ለህግ በማቅረብ በኩል በተደረገው የጋራ ጥረት 39 ተጠርጣሪዎች በህግ ጥላ ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

ሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች በማጋጨት አብሮ የመኖር እሴቶቻቸውን ለመናድ በተናጠልም ሆነ በግል በትንኮሳ ተግባር የሚንቀሳሱ የጥፋት ኃይሎችን ለህግ በማቅረብ በኩል ህዝቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለዜጎች መፈናቀል፣ ሞትና የንብረት መውደም እጃቸው አለባቸው ተብለው በህግ የሚፈለጉ ግለሰቦችም ሰላማዊ መንገድን በመምረጥ እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፌደራል፣ የክልሉና የዞኑ የጸጥታ ኃይሎች ለዜጎች ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅተው በመስራት የጀመሩትን ህግ የማስከበር ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም