የሱዳኑ ምክትል ፕሬዘዳንት ኦስማን መሃመድ ኢትዮጵያ ገቡ

120

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የሱዳኑ ምክትል ፕሬዘዳንት ኦስማን መሃመድ ዩሱፍ ኪቢር በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሃዘን ለመግለጽ ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ባለፈው እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በገጠመው የመከስከስ አደጋ የ157 ዜጎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

በዚህም የሱዳኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኦስማን መሃመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በሆነው አውሮፕላን ላይ በደረሰው የመከሰከስ አደጋና ህይወታቸው ባለፉ ዜጎች የሱዳን መንግሥትና ህዝብ የተሰማቸውን ሐዘን ለመግለፅ መምጣታቸው ተጠቁሟል።

ምክትል ፕሬዘዳንቱ ኦስማን መሃመድ በሱዳን መንግስትና ህዝብ ስም በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

የሁለቱን አገራት ህዝቦች የጠበቀ ግንኙነት ለማጠናከርና አገራቱ በዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተሳስረው እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ ምክትል ፕሬዘዳንቱ ሃዘናቸውን ለመግለጽ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ሁለቱ አገራት ያላቸውን ወዳጅነትና መልካም ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ምክትል ፕሬዘዳንቱ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም