አመራሩ ለወጣቱ ሥራ ዕድል ፈጠራና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ሊሰጥ ይገባል....የድሬዳዋ ነዋሪዎች

72

ድሬዳዋ መጋቢት 5/2011 የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አመራር ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ነዋሪዎች ጠየቁ።

አስተዳደሩ በቅረቡ ባካሄደው 2ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ አስቸኳይ ጉባኤው የምክር ቤቱን አፈ-ጉባኤ፣ ከንቲባዎችና አምስት የካቢኔ አባላትን አዲስ ሹመትና የሥልጣን ሽግሽግ ማድረጉ ይታወሳል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ሹመቱን አስመልክተው ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት አመራሩ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራና ለነዋሪው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የህዝብ ወገንተኝነቱ በተግባር ማረጋገጥ  አለበት።

ከነዋሪዎች መካከል ወጣት ናትናኤል ስዩም የስልጣን ሽግሽጉ የተሻለ ብቃት ያላቸውን ሰዎች በመጠኑ ወደ ፊት ያመጣ ቢሆንም ይጠበቅ የነበረው ያህል አለመሆኑን ተናግሯል፡፡

በአዲስ የተዋቀረው አመራር የወጣቱን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጥያቄ በተግባር መመለስ  እንዳለበት አመልክቷል፡፡ 

የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪ የሆኑት መምህርት መርሻዬ ባዩ በአዲሱ የተዋቀረው አመራር የነዋሪውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በእኩልነትና በፍትሃዊነት ሊመልስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ነዋሪው በብሔርና በጎሳ ተለያይቶ እንዲጣላና በከተማ አስተዳደሩ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሲሰሩ የነበሩ አመራሮች በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

አቶ አብዱረህማን ሙሜ በበኩላቸው " የነበሩት ሁሉም አመራር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለህዝቡ ተገቢ አገልግሎት ይሰጡ ያልነበሩና የበደሉ በመሆናቸው መነሳት ነበረባቸው " ብለዋል።

የተሻለ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ወጣቶችን ወደ አመራር ማምጣት የተሻለ ልማትና ዕድገት ለማስመዝገብ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመው አመራሩ በቀጣይ በወጣቱ ላይ ትኩረት አድርጎ አንዲሰራ ጠይቀዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ቦጋለች ገብሩ አዲሱ አመራር በከተማ አስተዳደሩ እየተስተዋለ የሚገኘውን ከቀበሌ ቀበሌ የመፈናቀል ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰርቶ መፍትሄ መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል።

አመራሩ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በድሬዳዋ በጊዜያዊ መጠለያ እየኖሩ የሚገኙ ዜጎችን ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ተንሳይ መንግስቱ በበኩላቸው "አመራሩ የሚፈልገውን ስኬት ማስመዝገብ የሚችለው የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ በመሆኑ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል" ብለዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ሰይፈዲን  ዩሱፍ አመራሩን ከቦታ ቦታ መለዋወጥና ማዟዟር ብቻ መፍትሄ የሚያመጣ ባለመሆኑ

በብልሹ አሰራር፣ በሌብነትና በሀብት ምዝበራ ውስጥ ያሉ አመራሮችን ተጠያቂ ማድረግና የህግ የበላይነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ አቶ ሰይፈዲን ዩሱፍ የተባሉ ሌላው የምክር ቤት አባል ናቸው።

"ተጠያቂነት ሳይኖር አመራሩን ከቦታ ቦታ መለዋወጥና ማዟዟር ብቻ መፍትሄ አያመጣም ሲሉም" ገልጸዋል።

አዲሱ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማሃዲ ጊሬ የተነሱት ጥያቄዎች በቀጣይ የሚታዩና መፍትሄ የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የሚፈለገው ለውጥና ውጤት እንዲመጣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ምሑራን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራትና በየደረጃው የሚገኙ ነዋሪዎች ከአስተዳደሩ ጎን በመሆን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አዳዲስ ሹመትና የስልጣን ሽግሽግ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም