ዛሬ ያልታመነ የፖለቲካ ፓርቲ ነገ መንግስት ሲሆን ሊታመን አይችልም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

132

አዲስ አበባ  መጋቢት5/2011 የቃል ኪዳን ሰነዱ ኢትዮጵያን የሚያተርፍና የሚያሻግር መሆኑን ማረጋገጥ  ይጠበቅበታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ዛሬ በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች የአሰራር ቃል ኪዳን ሰነድ ፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ሁሉም ፓርቲ ለህዝብ፣ ለሀገርና ለራሱም ጭምር መታመንና የኢትዮጵያን መፃኢ እድል በሚገነቡ የአንድነት ተግባራት ላይ ከወዲሁ መስራትና መለማመድ እንዳለበት ጠቁመው፤ "ዛሬ ያልታመነ የፖለቲካ ፓርቲ ነገ መንግስት ሲሆን ሊታመን አይችልም"  ሲሉም አፅንኦት ሰጥተው መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዛሬ በፊርማ የፀደቀው የስምምነት ቃል ኪዳን ሰነድ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ስምምነቶች በበለጠ  የተሰደዱ፣ ታስረው የነበሩና ለዛሬው የነጻነት አየር ፊት ለፊት ወጥተው መስዋዕትነትን የከፈሉትን ሁሉ ያሳተፈ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል  ብለዋል።

በመሆኑም ሰነዱ ሁሉም ፓርቲ በውስጡ የሚያምነውና የሚተገብረው ከዚህ ባለፈም በገለልተኛና በትውልድ አይን ሲታይ የማያሳፍርና የሚያኮራ መሆን አለበት ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  "አሁን ያለንበት ሁኔታ ነፃነት የተትረፈረፈበት፣ አንዳንዴም በስሜት የሚነዱ አካላት እንደመንግስት የሚተውኑበትና ነፃነት ያለበት እንጂ የጎደለ ነገር የለም" ያሉ ሲሆን፤ ነፃነቱን ባግባቡ ተጠቅመን ለሁሉም ዜጋ ጥቅም ልናውለውና ለቀሩት የአፍሪካ ወንድሞቻችን ምሳሌ የምንሆንበት መሆን ይገባል ብለዋል።

"በኦሮሚያ፣ በትግራይ ፣ በአማራ እና በሌሎች ክልሎች ባሉ ወረዳዎች የምትኖሩ ፓርቲዎችም ጭምር ክልሉ ወይም ወረዳው የኛ ብቻ ነው የሚለውን አስተሳሰብ አውጥታችሁ ከሁሉም ጋር አብራችሁ መኖር አለባችሁ" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ንግግሮች ላይ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዘርና በሌሎችም በመከፋፈል የምናደርሰው ኪሳራ ለሀገርም የሚተርፍ መሆኑን በማሰብ በትግስትና በመቻቻል በአብሮነት መስራት እንደሚጠበቅም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ከማዕከል እስከ ቀበሌ ያለው የኢህአዴግ አባልም ማንም ፓርቲ ሀሳቡን በነጻነት እንዲገልጽና ደጋፊዎቹን እንዲያወያይ ከቻለ ድጋፉን እንዲሰጥ፤ ካልቻለ ግን  ከማደናቀፍ በመቆጠብ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የመገናኛ ብዙሃኑም በተለይም በህዝብ ሀብት የምትንቀሳቀሱ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉንም ፓርቲዎች በእኩልነት፣ ግን ደግሞ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማስተናገድ አለባቸሁ ብለዋል።

ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በማምጣት ለፈለጉት ዓላማ የሚያውሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን መስራት እየፈለጉ እጅ ያጠራቸው መኖራቸውንም አልሸሸጉም።

ይህን ለማቀራረብም ፓርቲዎች "ተበትናችሁ ሳይሆን ሰብሰብ በማለት መንቀሳቀስ አለባችሁ፤ ምንጩ የማይታወቀውን ገቢ የሚታገኙ ፓርቲዎችም ጭምር ለጥፋት ሳይሆን ለልማት እንድታውሉ መንግስት የሚጠበቅበትን ይሰራል"  ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰብሰብ ብለው ለሚደራጁ የፖለቲካ ፖርቲዎች መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም