የመሰረታዊ ሸቀጦች ንረትና አቅርቦት ውስን መሆን ጫና ፈጥሮብናል... የሀድያ ዞንነዋሪዎች

76

ሆሳእና መጋቢት 5/2011 በሀድያ ዞን የመሰረታዊ ሸቀጦች ንረትና አቅርቦት ውስን መሆን በኑሯቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳና ሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ የሚኖሩት ወይዘሮ ውብአለም በየነ እንደተናገሩት በወረዳው የስኳርና ዘይት አቅርቦት ውስን መሆኑንና ወቅቱን ጠብቆ አለመግባቱ ለችግር እየዳረጋቸው ነው፡፡

ሸቀጡ በመንግስት በአግባቡ አለመቅረቡ በወረዳው በተለያዩ ሱቆች የሚቀርበውን ስኳርና ዘይት በውድ ዋጋ ለመግዛት እየተገደዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመንግስት በ75 ብር የሚቀርብላቸውን ባለ ሦስት ሌትር ዘይት እስከ 150 ብር እንዲሁም በ18 ብር ከ50 ሳንቲም ይገዙት የነበረውን አንድ ኪሎ ስኳር ከግለሰብ እስከ 50 ብር እየገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"በመንግስት ዘይትና ስኳር በወቅቱ ባለመቅረቡ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገናል፤ ይህም በኑሯቸው ላይ ጫና እየፈጠረብን ነው" ብለዋል።

በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚስተዋል የዋጋ ጭማሪ መንግስት ቁጥጥር ባለማድረጉ የተከሰተና በእዚህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን  ይበልጥ ተጎጂ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ በሆሳዕና ከተማ ሴች ዱና ቀበሌ የሚኖሩት አቶ ተሻለ አቢዮ ናቸው፡፡

ከሚያገኙት ወርሀዊ ገቢ ጋር ወጪያቸው እንደማይነጻጸር የገለጹት አቶ ተሻለ በሳሙና ዋጋ ሳይቀር ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

በከተማው የሊች አምባ ቀበሌ ነዋሪና በቀን ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ አልማዝ ረዳሀኝ በሚገዟቸው መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የፉርኖ ዱቄት አቅርቦት ጥሩ እንደነበርና አንዱን ኪሎ በ18 ብር በመግዛት ለዳቦ ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ዱቄት አስከ 40 ብር እየተሸጠ በመሆኑ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

መሰረታዊ ሸቀጦች ወቅቱን ጠብቀው የሚቀርቡ ካለመሆናቸው በተጨማሪ በውድ ዋጋ እየተሸጡ በኑሯቸው ላይ ተጽዕኖ እየፈጠሩ በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ፍቃዱ ኤርሱሞ በበኩላቸው "የሰዎች ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም እንዲሁም የጥሬ እቃ ዋጋ መጨመር የምርት ዋጋን ከፍ እንዲል በማድረግ የኑሮ ውድነት ያስከትላል" ብለዋል፡፡

በብዙ ብር ትንሽ እቃ ከተገዛ ብር የመግዛት አቅም እንዲያጣና ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ፍሰት በመፍጠር የኑሮ ውድነት እንዲከሰት የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"የሀድያ ዞን ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት ያለበት መሆኑ ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ ያደርገዋል" ሲሉም መምህር ፍቃዱ ገልጸዋል።

ይህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ መንግስት በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ችግር ፈጥኖ ሊፈታ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የሀድያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ሁንደሞ በበኩላቸው በዞኑ በመሰረታዊ እቃዎች ላይ የዋጋ ንረት መኖሩን አምነው ችግሩን ለመከላከል የዋጋ ቁጥጥር ኮሚቴ በማዋቀር ዝርዝር የመሸጫ የዋጋ እንዲለጠፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ነጋዴዎች ከተለጠፈው ዋጋ ውጪ ሲሸጡ ሕብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ተጠያቂ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ ትብብር ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በተለይ የዋጋ ንረት የታየባቸውን ሸቀጦችና ዕቃዎችን ለመምሪያው አልያም ለንግድና ልማት ጽህፈት ቤቶች በ8034 ነጻ የስልክ መስመር ደውሎ ሊጠቁም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በአን ሌሞ ወረዳ የስኳርና ዘይት አቅርቦት ውስን የሆነው በ1999 ዓ.ም በነበረው ህዝብና ቤት ቆጠራ የነበረውን ህዝብ ታሳቢ ያደረገ አቅርቦት በመኖሩና ይህም አሁን ካለው የህዝብ ብዛት ጋር ባለመጣጣሙ መሆኑን አስረድተዋል።

በየአካባቢው በቤተሰብ ብዛትና በተመዘገበው ቁጥር መካከል ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት ሲባል ዘንድሮ የሸቀጦች አቅርቦት መዘግየቱን ተናግረው በቀጣይ ሕብረተሰቡን የመካስ ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

በአካባቢው የስንዴ ምርት በመቀነሱ የዳቦ ዱቄት እጥረት እንደገጠመና በግል ፋብሪካዎችም ጭምር ዋጋው በመወደዱ የተነሳ ማቅረብ እንዳልተቻለ ገልጸው ችግሩን ለመፍታት ዱቄት ከሌሎች አካባቢዎች ለማስገባት በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ማንኛውም አይነት ጥያቄና ቅራኔ ሲኖረው መረጃ በመስጠት ህግ ወጥነትን በጋራ መከላከል እንደሚቻልም አቶ ታምራት አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም