በወላይታ ሶዶ ከተማ በግለሰብ ቤት የተከማቸ 24 ሺህ ሊትር ቤንዚን ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ ከተማ በግለሰብ ቤት የተከማቸ 24 ሺህ ሊትር ቤንዚን ተያዘ
ሶዶ መጋቢት 5/2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት በህገወጥ መንገድ የተከማቸ 24 ሺህ ሊትር ቤንዚን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አለማየሁ ቶማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ቤንዚኑ የተያዘው በከተማው የሕብረት ቀበሌ ነዋሪ በሆነ አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው።
ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ትላንት ጧት 2 ሰዓት ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ቤንዚኑ መያዙን ተናግረዋል።
ለጊዜው ከአካባቢው የተሰወረውን የቤቱን ባለቤት ፖሊስ በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ ለማቅረብ ክትትል እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሌላ ዜና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ 10 ኩንታል ስኳርና 45 ባለ 25 ሊትር ዘይት በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ውሏል።
የቅርንጫፉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰልማን ዳውድ ለኢዜአ እንደገለጹት ትላንት እኩለ ቀን አካባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ መከ-09595 ኦራል የመከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪ በህገ-ወጥ መንገድ ስኳርና ዘይቱን ሲያዘዋውር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ከወልድያ ወደ ቆቦ መስመር ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር የዋለው በወልድያ የፍተሻ ጣቢያ መሆኑንም ተናግረዋል።
አሽከርካሪውን ጨምሮ አብረው የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ በመጣራት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡