ትኩረት የሚሻው ጉዳያችን…

107

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ከተግባሩና አላማው አንጻር ሲታይ መንፈሳዊና አገራዊ ጥበብ የተላበሰ ግዴታ  ነው፡፡ ህዝብና ቤቶች ቆጠራ ሲካሄድ ዋነኛ መነሻው በአንድ አገር ያሉ ዜጎች ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ፣ እንማን እንደሆኑ እና በየት አካባቢ እንደሚኖሩ የምናውቅበት መሳሪያ እንደሆነ ከአለም አቀፍ ህዝብና ቤት ቆጠራ እአአ 2015 እስከ 2024 የተዘጋጀ ፕሮግራም ያስረዳል። ከዚህም ጋር ተያይዞ  የአንድ አገር አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር በየአስር አመቱ መቆጠር እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ህዝብ ፖሊሲ ያስገድዳል።

በተጠቀሱት አመታት አጠቃላይ የህዝቡን ቁጥር በማወቅና ለቁጥሩም የሚመጥን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና እና ማህበራዊ ስራዎችን በተገቢው ሁኔታ ለመስራት ያመች ዘንድ ነው። ለሀገራችንም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ሀገራዊ እቅድ የሚዘጋጀው፣ ትምህርቱ የሚስፋፋው፣ ጤናው የሚጠበቀው፣ ልማቱ የሚካሄደው ወዘተ፣ በህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መረጃዎች ላይ በመመስረት ነው፡፡ ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲካሄድ፣ የማንነት ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉት፣ የህዝብ ውክልናዎች የሚታወቁት በዚሁ መረጃ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ 4ኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ በዚህ ወር መጨረሻ ለማካሄድ ፕሮግራም እንደተያዘለት ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል። ይህ አሰራርና ኹነት ለአገሪቱ የወደፊት እቅድም ሆነ የልማት ስራ ዋና መሰረት መሆኑ ታምኖበታል፡፡

የህዝብና ቤቶች ቆጠራና አለም አቀፋዊ ተሞክሮ

በአሜሪካን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝብና ቤቶች ቆጠራ የተደረገው እ.ኤ.አ 1790 በ22 የህዝብና ቤት ቆጠራ መስሪያ ቤቶች በመታገዝ በቶማስ ጀፈርሰን አስተባባሪነት እንደ ነበር ከአለም አቀፍ ህዝብና ቤት ቆጠራ ድረ- ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

በአሜሪካ ህግ መተዳደሪያ ኮደ 13 በተሰኘ አንቀጽ አማካኝነት አጠቃላይ አገራዊ ቆጠራው እንዴት እንደሚካሄድ እና መረጃውም ሚስጢራዊነቱን ጠብቆ እንዴት እንደሚያዝ የሚያብራራ ህግና ስርዓት የያዘ ነበር። በሚደረገው ማህበረሰባዊ ዳሰሳ አማካኝነት ለሚጠየቁ ማንኛውንም ጥያቄዎች አልመልስም ወይም ቸልተኝነት ያሳየ ግለሰብ አንድ መቶ የአሜሪካን ዶላር ሲቀጣ፣ ለንግድ ቦታዎችና በንግዱ ዘርፍ ትክክለኛ ስም አለመስጠት ደግሞ 5 መቶ የአሜሪካን ዶላር ሲጣልበት አጠቃላይ አገራዊ መረጃን ግን በስህተት መናገር ከሆነ ደግሞ 10 ሺ የአሜሪካን ዶላር ቅጣት እንደሚጣልበት በህጉ ላይ ተቀምጧል።

እአአ በ1970 በተደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ 16 በመቶ ያህሉ ጥቁር አሜሪካዊ እና 2 በመቶ የሚሆኑ ነጭ አሜሪካዊ በወቅቱ እንዳልተቆጠሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአሜሪካ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ዘንድ ከሚቀነቀኑ ርዕሶች መካከል የህዝብና ቤቶች ቆጠራ አካሄድ የበለጠ ተዓማኒነቱን ለመጨመርና  የተሟላ መረጃ ለማግኘት  ዘመናዊ የናሙና አወሳሰድ ዘዴን እንከተል ሲሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ ሪፐብሊካኖች የሚደረገው አገራዊ ህዝብና ቤቶች ቆጠራ የአሜሪካ ህገ መንግስት የሚፈቅደውን በህዝብ ቁጥር የመወከልን ስልትና አሰራርን መከተል አለብን ሲሉ ይሞግታሉ።

በየአስር አመቱ የሚካሄደው ይህው የአሜሪካ ህዝብና ቤት ቆጠራ አጠቃላይ አላማው የህዝብን ቁጥር ከማወቅ በተለየ ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ለማድረግ፣ በህዝብ ቁጥር አማካኝነት እያንዳንዱ የአሜሪካ ግዛት ትክክለኛ ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲያገኙ ለማድረግ እናም በአጠቃላይ የጾታውንና የዕድሜውን ስብጥር ለማወቅ እንደሚጠቀሙበት ከአሜሪካ ሴንሰስ ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ይህንንም አገራዊ ህዝብና ቤት ቆጠራ እውን ለማድረግ ከፌደራል ተቋማት ጀምሮ እስከ ግዛቶች ድረስ የሚደርስ መዋቅራዊ አሰራርን ያካተተ የሲቪክ ማህበራት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የፍትህ ተቋማትና የሁሉንም ዜጋ ትብብርን መሰረት ያደረገ አካሄድ ነው ያላቸው።

በሌላ በኩል አፍሪካን  ጨምሮ ሌሎች አገራት በቅኝ ግዛት ወቅት በአገራቱ ፍላጎት ባይሆንም እአአ ናይጄሪያ 1866፣ ሱዳን 1955 ቆጠራ ሲያካሂዱ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዩባክስቲካን፣ ማዳጋስካር  እና የመሳሰሉት አፍሪካን አገራት እአአ እስከ 1990 ምንም አይነት ህዝብና ቤቶች ቆጠራ አለማድረጋቸውን ነው የኢትዮጵያ ስታቲስሺያን ማህበር ፕሬዚደንት የሆኑትዶክተር መርጋ በሊና የተናገሩት። እንደ ዶክተሩ ገለጻ በዚያን ወቅት አጠቃላይ የአፍሪካ አገራት  ነጻነታቸውን ያላገኙበት ወቅት ሰለነበር እ.ኤ.አ እስከ 1950ዎች በዴሞግራፊካል ሳምፕል ሰርቬይ  (Demographic Sample Survey) በመታገዝ ብቻ ነበር ዳሰሳ የሚያደርጉት።

የኢትዮጵያ ህዝብና ቤት ቆጠራ ታሪካዊ ዳራ

በኢትዮጵያ በደርግ ዘመነ መንግስት በ1976 ዓ.ም የጀመረው የህዝብና ቤት ቆጠራ በኢህአዴግ መንግስት ደግሞ በ1987 እና በ1999 ዓ.ም ሁለተኛውና ሶስተኛው ቆጠራዎች  ተካሂደዋል። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 103 የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽንን ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን አካል አድርጎ ‹‹ያቋቁማል››፡፡ በ1985 ዓ.ም. በወጣው የሕዝብና የቤት ቆጠራ ኮሚሽን ሕግ ተፈጻሚነት መሠረት በኢትዮጵያ በየአስር አመቱ መካሄዱን ቀጠለ። ነገር ግን እንደገና  በ1991 ዓ.ም. የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን አዲስ  ማቋቋሚያ ሕግ ‹‹በየአሥር ዓመቱ አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራ›› ማከናወንን ዘላቂ የመንግሥት ሥራ እንደሆነ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ  ኤጄንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።  

ምንም እንኳን በየአስር አመቱ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ቢካሄድም በ1997ዓ.ም መደረግ የነበረበት ቆጠራ በሁለት አመት ተራዝሞ በ1999 መደረጉ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል። ከዚያ በኋላም ልክ በ10 አመቱ በ2007 መደረግ የነበረበት ቢሆንም ባለፉት አመታት በአገሪቷ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ሲጎተት ቆይቶ አሁን በዚህ አመት ለመደረግ ፕሮግራም ተይዞለታል። በመሆኑም አገራዊ ህዝብና ቤቶች ቆጠራ እየጨመረ የመጣውን ፍትሃዊ የሀብት ስርፅትን ከማሳለጡም በተጨማሪ በፖለቲካው ረገድም በህዝብ ተመጣጣኝ የሆነ ውክልና እንዲኖር ያግዛል። እናም የመጪዎቹ አሥር ዓመታት የተለያዩ የልማት ፖሊሲዎች የሚቀረጹበት በመሆኑ  የዘንድሮውን ህዝብ እና ቤቶች  ቆጠራ መረጃና ወደፊት በየጊዜው የሚሰጡትን ትንበያዎች መሰረት አድርጎ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡

የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትና አገራዊ ፋይዳው

የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የመጀመሪያው ጥቅሙ የህዝብን ቁጥር ከማወቅ በዘለለ አገራዊ ፖሊሲንና ስትራቴጂን ለመንደፍ ዋነኛ መሳሪያ ነው። ፍትሃዊ እና ትክክለኛ የሆነ የህዝብ ቆጠራ ደግሞ መረጃን በትክክል መሰብሰብ፣ መቁጠርና ማደራጀትን የሚያካትት እንደሆነ  ዶ/ር መርጋ በሊና ያስረዳሉ። እንደ ሀላፊው ማብራሪያ የህዝብና ቤት ቆጠራው በሶስት አይነት ሂደት ማለትም ከቆጠራ በፊት፣ በቆጠራ ወቅትና ከቆጠራ በኋላ የሚገኙ መረጃዎችን በጥንቃቄና ሀላፊነት በተሞላበት  መልኩ መካሄድ አለበት።

ቴክኖሎጂን በመጠቀም  ቆጠራውን ባካሄዱ ሀገሮች ተሞክሮ ላይ ተመስርቶ ይህ አራተኛው ህዝብና ቤቶች ቆጠራ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚካሄድ ነው። በዚህ ቴክኖሎጂ ተአማኒነት ያለው ቆጠራ በመላ ሀገሪቱ ለማካሄድ እንደሚያስችል የታመነበት ሲሆን፣ በዚህም ባለፉት ቆጠራዎች የታዩ ቅሬታዎች በድጋሚ ሊከሰቱ የሚችሉበት እድል እንዳይኖር የሚያስችል መሆኑም ነው የሚነገረው።

ቆጠራው የህዝቦችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና መረጃ በትክክል በማሟላት መንግስት በየጊዜው የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና አስትራቴጅዎች ተግባራዊ በማድረግ የተረጋጋች ሀገር ለመመስረትና ለመገንባት ብሎም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ይረዳል።  በሚገኘው መረጃም ተጠያቂነትና ግልፅነት ያለው የመንግስት አሰራር ለመፍጠር፤ ጥራቱ የተጠበቀ ትምህርት አግኝቶ ያደገና ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል እቅድና ፖሊሲ ማውጣት የሚችለው የህዝብና ቤት ቆጠራን ውጤት ተንተርሶ ብቻ እንደሆነም ይታመናል።  

የቆጠራው ውጤት በንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት፣ በንግድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በብድር አገልግሎት ወዘተ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ የሚያስችለውም ፕሮግራምና እቅድ የሚተለመው የህዝብና ቤት ቆጠራን ውጤት መነሻ በማረግ ነው ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተርና የቆጠራ ኮሚሽን አቶ  ቢራቱ ይገዙ ናቸው።  

እንደ ሀላፊው ማብራሪያ ቆጠራው እንዳለፉት ጊዜያት ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድ ሲሆን፤ ከምንም በላይ ደግሞ ቆጠራው በአምስት የአገሪቷ ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማሊኛና በአፋርኛ  የሚካሄድ መሆኑ የመረጃ ሰብሳቢዎች እና ተቆጣጣሪዎች እምነትና አመለካከት ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም ህብረተሰቡ ሳይቸገር እና አስተርጓሚም ሳያሻው ሁሉንም መረጃዎች በትክክል ለመመዝገብ ያስችላል።

ቆጠራው ከፊታችን መጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 20/ 2011 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ሲሆን ለቆጠራው ወደ 200ሺ የሚሆኑ የቆጠራ ጣቢያዎችና 152ሺ የቆጠራ ማእከላት መዘጋጀታቸውን ነው ሀላፊው ያስረዱት። በዚህም 152ሺ ባለሙያዎች፣ 38 ሺ ተቆጣጣሪዎች እና 180 ሺ ታብሌት ኮምፒውተሮች እንዲሁም ኤሌክትሪክ ቢጠፋም ብሎም ቢቋረጥ ተክተው ሊሰሩ የሚችሉ ተንቀሳቃሽ ቻርጀሮች እንደተዘጋጁም ታውቋል።

የህዝብ ቁጥርን ማወቅ የቆጠራው ዋናው አስፈላጊ ጉዳይ  ተደርጎ ቢወሰድም፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ህዝብ ምን ያህል ስለመሆኑ፣ ስለዕድሜ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የመኖሪያ ቤት፣ ወዘተ ዝርዝር መረጃ የሚሰበሰብበት ነው፡፡ ዘመናዊ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መረጃ ለምርምር ፣ ለንግድ ሥራ፣ ለእቅድ፣ ወዘተ ይጠቅማል፡፡ በምርጫ ወቅትም የህዝብን ወኪሎች ለመለየት ያገለግላል፡፡

ቆጠራ ለአንድ አገር ልማት እና እድገት ትልቅ ትርጉም እንዳለው የሚጠቅሱት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ናቸው፡፡  እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ የመንግሥትን አገልግሎት ወደ ህዝቡ ለማድረስ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ በጀት ለመመደብና ልማትን ለማምጣት ሀገሪቱ ያላትን የህዝብ ቁጥር ማወቅ ሊዘለል የማይችል ተግባር ነው። መንግሥት የህዝቡን ቁጥር ካላወቀ ከየት ተነስቶ ወደየት እንደሚደርስ፣ ለየትኛው ህብረተሰብ ምን አይነት አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ለማወቅ እንደሚቸገርም ያብራራሉ፡፡

እነዚህን እና መሰል ስራዎችንና እቅዶች ለማሳካት፤ ሥራው በምን አይነት ሁኔታ እየሄደ ነው የሚለውን ለመከታተል የግድ የህዝቡን ቁጥር ማወቅ ያስፈልጋል ሲሉ ፕሮፌሰር ጣሰው ይጠቅሳሉ፡፡ «ተደራሽነትን ለመለካት የህዝብ ብዛት መጠን በትክክል መታወቅ ይኖርበታል›› የሚሉት ፕሮፌሰር ጣሰው፣ አሁን ግን “የህዝቡን ቁጥር ካለማወቅ የተነሳ አንዳንድ የስታትስቲክስ መረጃዎች እየተፋለሱ ይገኛሉ፡፡  የትምህርት ቅበላን ለአብነት በመውሰድም፣ ቅበላው ከመቶ በመቶ በላይ ሄዷል” እየተባለ እንደሚገለጽ ይናገራሉ፡፡ ይህም የህዝብ ቁጥሩ በትክክል አለመለካቱን እንደሚያሳይ ነው የሚያስረዱት፡፡

የአገሪቷን የህዝብ ቁጥር በትክክል አለማወቅ በርካታ አገራዊ ቅሬታዎች እንዲነሱ ከማድረጉም በላይ፤ ለአላስፈላጊ ለጭቅጭቆችና ለስህተት እንደሚዳርግ በመጥቀስ፣ የተጣጣመ ሥራ ለመሥራት የህዝቡ ቁጥር በትክክል ሊታወቅ ይገባል ይላሉ፡፡

በህዝቡ ውስጥ ያሉ  ብዥታዎች

ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት ለሦስት ጊዜ ያህል የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራን አካሂዳለች፡፡ ከተካሄዱት  የሕዝብና ቤቶች ቆጠራዎች በ1976 ዓ.ም እና በ1987 ዓ.ም የተደረጉት ሁለት ቆጠራዎች እስከ ችግራቸውም ቢሆን ዓለማቀፋዊ ሕጉን የተከተሉ ነበሩ፡፡ እናም የመጀመሪያው የህዝቡ ጥርጣሬ እና ብዥታ ቆጠራው ከተለያዩ ችግሮች ተላቆ በትክክል ይካሄዳል  ወይ የሚለው ስጋት አንዱ ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ካደረገቻቸው የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የተሻሉ ነበሩ ያሉት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕላን ኮሚሽን የሥነ-ሕዝብ ጥናት እና መረጃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታደለ አሳቤ ናቸው። ለዚህ ማሳያው በ1999 ዓ.ም የተደረገው አገራዊ የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ‹‹ፖለቲካዊ ይዘት የነበረው፤ ለግላዊ ጥቅም እንጂ ያለውን አጠቃላይ ጠቀሜታ ታሳቢ ያላደረገ ነበር›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም በስህተትም፤ ሆነ ተብሎም የሚፈጠሩ ችግሮች መረጃን ከማዛባታቸው በላይ ማንኛውንም ዜጋ የመቆጠር አለም አቀፋዊ መብቱን የሚነፍግ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በሀላፊነትና በእኔነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ሀላፊው በአጽዕኖት የተናገሩት።

ሌላኛው የህዘቡ ስጋት ደግሞ ሌሎች ተንቀሳቃሽ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለምሳሌ  አርብቶ አደር፣ በቅርቡ ለዘመናት ይኖሩበት የነበረው ቦታቸውን ትተው በየቦታውና በየመጠለያ ካምፕ የሚገኙ የተፈናቀሉ  ህብረተሰችን እንዴትና በምን ሁኔታ ይቆጠራሉ የሚለው ነው። የቆጠራ ኮሚሽን ሰብሳቢና የኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዳመለከቱት በተለይ የተፈናቀሉ ዜጎችን በቀሩት ቀናት በመታገዝ ወደነበሩበት ቦታ እንመልሳለን ማለታቸውም የሚታወስ ነው። ነገር ግን በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል ወይ የሚለው እራሱን ችሎ ጥያቄ ነው። በክልሎች በየደረጃው የሚገኙ አደረጃጀቶችንና የመንግስት መዋቅሮችን በመጠቀም በተለይ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ በቆጠራው ሰሞን ውስን ጊዜ በመሆኑ ወደ መደበኛ መኖሪያቸው ወደሆነው አካባቢ መልሶ በማምጣት የሚቀጠሩበትን ስርዓት መፍጠር ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ በተለይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከአፋር፣ ከደቡብ፣ ከኦሮሚያ እንዲሁም ከሱማሌ ክልሎችና ከሌሎች ጋር በዚሁ አግባብ እየሰሩ እንደሆነ ነው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ሀለፊ ያስታወቁት፡፡

በአሁኑ ወቅት ሌላው የሁሉም ማህበረሰብ ስጋት የሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ  ውዥንብሮች እና የሃሰት ወሬዎች ናቸው፡፡ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ማለት የህዝቡን ቁጥር በፆታና በዕድሜ መረጃውን ሰብስቦ እና አቀነባብሮ ውጤቱን ከማቅረብ የዘለለ ሌላ ምንም አይነት የተለየ አጀንዳ የለውም፡፡ አሁን አሁን ግን  በግልጽም በድብቅም እየታየ የመጣው ጫፍ የነካ ብሄርተኝነት ከስጋቶቹ አንዱ ነው። ይህ ጉዳይ የብሄርን ቁጥር አብልጦ ማሳየት እና የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውክልና በቁጥሩ ልክ የመወከልን ፍላጎትና አዝማሚያ የሚያሳይ ነው። በትክክኛው አካሄድ ቢሆን ባልከፋ ነበር፤ በተጭበረበረ እና ህጉን ባልጠበቀ የሚከሄደው አካሄድ ልክ አለመሆኑንም ሀላፊው አስረድተዋል። ይህንን ብዥታ ለመፍታትም ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመስራት ትክክለኛውን መረጃ መስጠት ያስፈልጋል።  

ቆጠራው በአገሪቱ ትክክለኛ የልማት እቅዶችንና ፖሊሲዎችን በመቅረፅ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችል እንጂ ሌላ የተለየ አጀንዳ የለውም በማለት የተናገሩት ደግሞ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የኦሮሚያ የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ሼኮ ጉሩ ናቸው። ቆጠራው በትክክልና በጥራት መካሄድ የአገሪቷን ሁለንተናዊ ተጨባጭ ሁኔታ በማመላከት ከሀገር ባሻገር ዓለም አቀፍ ፋይዳውም የጎላ በመሆኑ መረጃው በትክከል መሰባሰብ እንዳለበት ኃላፊው ይገልጻሉ።  

ሌላው ትልቁ ስጋት ደግሞ በከተማ አካባቢ የሚያከራዩ ግለሰቦች ‘ተካራዮች ቤት ይወስዱብናል’  በሚል በተሳሳተ እሳቤ ተከራዮቹን ለማስመዝገብ ፍቃደኛ የማይሆኑበት ሁኔታ ስላለ ከወዲሁ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሁሉ ማስረዳት እንድሚጠበቅም ነው አቶ ሼኮ  የጠቀሱት።

ቆጠራውን ለማካሄድ የባለ ድርሻ አካላት ሚና

ለ4ኛ ጊዜ ለሚካሄደው  ህዝብና ቤቶች ቆጠራ 9 ሚኒስትሮች፣ 8 የክልል ም/ርዕስ መስተዳደሮች ፣ 2 ክንቲባዎች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ  በድምሩ 20 አባላትን የያዘ የቆጠራ ኮሚሽን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰይሟል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሰብሳቢነት የሚመራው ይህው ኮሚሽን ዋናው ሀላፊነት አጠቃላይ የቆጠራውን ሂደት በመከታታል ለሚፈጠሩ ክፍተቶችና ችግሮች ድጋፍና ክትትክል በማድረግ ለተግባራዊነቱ መረባረብ እንደሆነ መተዳደሪያ ደምቡ ያስረዳል።

በኮሚሽኑ እንደ ባለድርሻ አካላት ከተያዙ ተቋማት መካከል የፌዴራል መንግስት፤ በየደረጃው ያሉት መዋቅሮች፣ የደህንነት መስሪያ ቤት፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የየክልሎች መንግስታትና ማዘጋጃ ቤቶች፣ የግል ድርጅቶችና መስሪያ ቤቶች፣ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት፣ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሙያና ሲቪክ ማህበራት፣ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም መላው ዜጎች ናቸው። በመጨረሻም ይህ በቴክኖሎጂ ዕገዛ የሚደረገው 4ኛው አገራዊ ቆጠራ በተያዘለት መርሀ ግብር ይካሄድ ዘንድ የመገናኛ ብዙኃን በቆጠራው ፋይዳ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዋናነት በቴክኖሎጂ መታገዙ ችግሩን ይቀንሰው እንደሆነ እንጂ ማስቀረት ስለማይችል የቆጣሪዎችም ሆነ የተቆጣሪዎች ከምንም አይነት ፖለቲካዊም ሆነ ጎሳዊ ማንነታቸው ራሳቸውን አውጥተው ለህሊናቸው ብቻ በመገዛት መስራት ይጠይቃል።   የተለያዩ ዘርፎች ባለሙያዎች በህዝብና ቤቶች ቆጠራ መረጃዎች ፋይዳ ላይ ትንታኔዎችንና ማብራሪያዎችን እንዲሰጡ በማድረግ ግንዛቤ የማስፋቱን ተግባር ሚዲያዎቹ አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

ህዝቡም ቢሆን ተገቢውን መረጃ በመስጠትና ተገቢ ያልሆነ ነገርም ሲያይ በወቅቱ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሪፖርት በማድረግ፤ በኋላ የሚመጣው መዘዝ ከወድሁ መግታት ይገባል፤ ይህም ለቆጠራው ስኬት ከግለሰብ አንስቶ የሁሉም ወገን ኃላፊነት ነውና ሃላፊነታችን እንወጣ እንላለን፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም