የጊዳሚ ሆስፒታል በባለሙያ እጥረት የሚጠበቅበትን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም

1777

ጊዳሜ ግንቦት 23/2010 በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ከተማ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የጊዳሚ ሆስፒታል በባለሙያ እጥረት የሚፈለገውን ያክል አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ጤና ጥበቃ ቢሮ በበኩሉ ችግሩ ባለፈው ዓመት  የበጀት እጥረት በማጋጠሙ ባለሙያዎችን መመደብ አለመቻሉን ገልጿል።

በሆስፒታሉ ለህሙማን አገልግሎት እንዲሰጡ የተገዙ የተለያዩ የመመርመሪያ ማሽኖችም በሰው ኃይል እጥረት አገልግሎቱን እየሰጡ አለመሆናቸው ተጠቁሟል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቢኒያም ዳዊት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተገሩት የጊዳሚ ሆስፒታል ባለፈው 2009 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቀዶ ጥገና፤ የሲኤሲ፤ የላፓራቶሚና የቀዶ ጥገና አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።

በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው ለመታከም ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት በከፍተኛ መጠን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ሆስፒታሉ ባለበት የባለሙያና የሰው ኃይል እጥረት የሚፈለገውን ያክል አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት እየፈጠረበት መሆኑን ነው የሆስፒታሉ ባለሙያዎች  የሚያስረዱት።

ዶክተር ቢኒያም ዳዊት የጊዳሚ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር“ትልቅ ችግር ያለብን የሰው እጥረት ነው፤ አንድ ነርስ ሁለት ቦታ ሶስት ቦታ የሚሰራበት ሁኔታ አለ፤ ሜዲካል ዋርደር ሆኖ ይሰራል፣  ያክማል እንዲሁም መርፌ  ይሰጣል”ብለዋል፡፡

አቶ ኩምሳ ረቡማ በጊዳሚ ሆስፒታል የነርስ ባለሙያ እንዳሉት “እየሰጠን ያለነው የህክምና አገልግሎት በጣም ጥሩ ነው፤ ሆኖም የሰው ኃይል እጥረት አለብን በዚህም ሳቢያ ብዛት ያላቸውን ታካሚዎች ለመርዳት በሚደረገው ጥረት በሰዓት መውጣት አልቻልንም። በአንድ ሰው ላይ የስራ ጫና እንዲኖር አድርጓል። ስለዚህ መንግስት የሰው ኃይል በመጨመር ችግሩን እንዲፈታልን እንጠይቃለን።”

 

ባሉት ባለሙያዎች አብቃቅቶ ለመስራት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር ቢኒያም፤ ችግሩ ጊዜ የሚሰጠው ባለመሆኑ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ለህሙማን አገልግሎቱን  ለመስጠትም ትልቅ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም ባለሙያዎች በየሆስፒታሎች ሲመደቡ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ከመመደብ አንጻርም ክፍተቶች መኖራቸውንም ነው ሜዲካል ዳይሬከተሩ የሚናገሩት።

“  አዲስ አበባ አካባቢ ወይም ትንሽ ከተማ ሆስፒታል ብትወስድ ቢያንስ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ 40 እስከ 50 ነርሶች ነው ያሉት እኛ ጋ ግን 22 ነርሶች ነው ያሉን ፤  አንዱ ስለፈለገ ብቻ የፈለገበት ቦታ መመደብ አለበት ብዬ አላምንም።”

በኦሮሚያ ጤና ጥበቃ ቢሮ የሰው ኃይል አስተዳደር ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ ደረጀ አዱኛ  በበኩላቸው ችግሩ የተከሰተው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመደቡ ባለሙያዎች አናሳ መሆንና የበጀት እጥረት በክልሉ አጋጥሞ ስለነበር መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የጊዳሚ ሆስፒታልን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት ስራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ ትልቅ እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል።

በቀጣይ በ2011 በጀት ዓመት ችግሩን ለመቅረፍ ጊዳሚ ሆስፒታልን ጨምሮ ለሌሎች አዳዲስ ሆስፒታሎች ቅድሚያ በመስጠት ባለሙያ የማሟላት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የባለሙያ እጥረት ያለባቸውን የጤና ተቋማት በመለየት ከመንግስት ከሚመደቡ ባለሙያዎች በተጨማሪ ክልሉ በራሱ ከግል የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ  ባለሙያዎችን በመቅጠር የሰው ኃይል የማሟላት ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮም ለፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል መጠን የማሳወቅ ስራ ሰርቶ ችግሩን በጋራ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።