አሜሪካ ሁሉም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ አገደች

687

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 አሜሪካ ሁሉም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ አገደች።

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ባሳለፍነው እሁድ ተከስክሶ ለ157 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ከሆነ በኋላ  በአውሮፕላኑ ላይ እየተነሱ ባሉ የደህንነት ስጋቶች ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዕዛዙን እንዳስተላለፉ ነው የተገለጸው።

በመሆኑም ሁሉም የቦይንግ 737 ማክስ 8 እና ማክስ 9 አውሮፕላኖች ከበረራ በአስቸኳይ እንዲታገዱ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

ሁሉም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ ያደረገውነው ለአሜሪካ ህዝብና ለሌሎች ህዝቦች ደህንነት ሲባል ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት የአሜሪካው የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር ቦይንግ 737 ማክስ የተሰኙ አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ በአሜሪካ አየር መንገዶች ጥቅም ላይ እንዳይውል እና አውሮፕላኑ በአሜሪካ የአየር ክልል ውስጥ እንዳይበር ትእዛዝ አሳልፏል።

በመሆኑም  የአሜሪካ አየር መንገዶችና የአውሮፕላን አብራሪዎች የእገዳው መልእክት እንደደረሳቸው እና አውሮፕላኖቹ በደረሱበት ቦታ እንዲቆሙ ትእዛዝ ማስተላለፉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተከሰከሰበት ስፍራ እና ከሳታላይት ላይ የተገኙ አዳዲስ መረጃዎች ላይ በመመስረት ከዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱንም የአቪየሽን አስተዳደሩ አስታውቋል።

የቦይንግ ኩባንያም ከብዙ ማመንታት በኋላ ሁሉንም የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ከዓለም አቀፍ በረራ አግዷል።

በመሆኑም አሜሪካዊው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ወደስራ የገቡ 371 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ከበረራ አግዷል።

የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር አውሮፕላኖቹ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ ውሳኔ ማሳለፉም የአሜሪካ አየር መንገድ ሰራተኞችን አስደስቷል።

የአሜሪካ የትራንስፖርት ሰራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጆን ሳሙየልሰን እንደተናገሩት፥ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ እንዲወጡ መወሰኑ በአውሮፕላን ለሚጓዙትም ሆነ ለአቪየሽን ሰራተኞች መልካም ዜና ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በርከት ያሉ አየር መንገዶች ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖችን ማገዳቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ እና ቻይና በቀዳሚነት አውሮፕላኖቹን ማቆማቸውን የገለፁ ሲሆን፥ ብሪታኒያና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና አውስትራሊያ፣ ህንድ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ብራዚል፣ ኖርዌይ፣ ኢንዶኔዢያ እና ማሌዢያ አውሮፕላኑን ከከለከሉት ሀገራት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

ሀገራቱ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰናቸውን ተከትሎም ኩባንያው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ነው የተባለው።