በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መስፋፋት ሰፊውን ድርሻ ይይዛል

583

መጋቢት 5/2011 ህብረተሰቡ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራሱን እንዲጠብቅ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የስኳር ህመም ሃኪም ዶ/ር ጌታሁን  እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቀዳሚ የጤና እክል ያልነበሩት የስኳር ህመም የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአሁኑ ወቅት የበርካታ ወገኖችን ህይወት እየቀጠፉ ነው፡፡

ዶ/ር ጌታሁን  ለበሽታው መስፋፋት እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቅሱት በሀገሪቱ ከከተሞች እድገት ጋር ተያይዞ በከተማ ያለው ያልተስተካከለ የኑሮ ዘይቤ እና አነስተኛ  የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ባህል ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው፡፡

አብዛኞቹን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች  በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ  በማድረግ እና   የአመጋገብ ስርዓትን በማስተካከል መከላከል እንደሚቻል የሚመክሩት ዶ/ር  ጌታሁን  ህብረተሰቡ በየዕለቱ ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት ይላሉ።   

በከተሞች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በማስፋፋት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለውን ፋይዳ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወን እንዳለበትም ዶክተሩ ሳይገልጹ አላለፉም።

“ከዚህ ቀደም ስፖርት የመስራት ባህል ስላልነበረኝ ለአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ተጋላጭ ብሆንም ተመርምሬ ራሴን ካወቅኩበት እለት አንስቶ ግን በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የስኳር በሽታየን መቆጠጠር ችያለሁ“ ያሉት ደግሞ አቶ ኢሳያስ አሮን ናቸው፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ  የተለያዩ ሽታዎችን ከመከላከል  ባሻገር፤ የጤና እክል ያላቸው ሰዎችም ጤናቸውን  ለማሻሻል ይረዳል ሲሉም አቶ ኢሳያስ  ልምዳቸውን አካፍለዋል።

“መንገድ ለሰው” በሚል መሪ ሃሳብ መንገዶችን ከትራንስፖርት ነፃ በማድረግ የስፓርታዊ እንቅስቃሴዎች እናድርግ የሚል መርሃ ግብር በማውጣት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ  ገልጿል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አለማየሁ ሁንዱማ እንደሚሉት በከተማዋ ወደ ጤና ተቋማት ለህክምና የሚመጡ ታማሚዎች 50 ከመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ነው፡፡

የመርሃ ግብሩ ዋና ዓላማም ህብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ጤናውን እንዲጠብቅ እና በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስከ አሁንም መርሃ ግብሩ በከተማዋ የሚገኙ 5 ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በቀጣይ በመላው የከተማዋ አከባቢዎች ለመተግበር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ በሚደረግበት ወቅት የትራንስፖረት አገልግሎት ሰጪዎችም ሆነ ተጠቃሚዎች የመርሃ ግብሩን ዓላማ በመረዳት ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባም ሃለፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ  ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው በወር አንድ ግዜ መንገዶችን ከተሽከርካሪ ነጻ በማድረግ፤ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ መርሃ ግብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተጠቁሟል።