ቦይንግ በመላው ዓለም የሚገኙ 737 ማክስ የተሰኙ አውሮፕላኖቹን በረራ እንዳያደርጉ ወሰነ

63

መጋቢት 5/2011 የአሜሪካ አቪየሽን አስተዳደር መርማሪዎች በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ዙሪያ አዲስ ማስረጃ አግኝተናል ማለታቸውን ተከትሎ ቦይንግ በመላው ዓለም የሚገኙ 737 ማክስ የተሰኙ አውሮፕላኖቹን በረራ እንዳያደርጉ ወሰነ።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደሩ አደጋው በደረሰበት ቦታ ባደረገው ምርመራና ባገኘው አዲስ መረጃ መሰረት ቦይንግ አውሮፕላኖቹን በአስቸኳይ እንዲያግድ ማዘዝ አለበት ብለው ነበር።

የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ (ቦይንግ) 737 ማክስ 8 እና 9 የተሰኙ ከ371 በላይ አውሮፕላኖችን በረራ እንዳያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር እንዳለው አዲስ ማስረጃና ግልፅ የሳተላይት መረጃዎችን በማግኘቴ ቦይንግ  737 ማክስ አውሮፕላኖች ለጊዜው መታገድ አለባቸው ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንገ 737 ማክሰ 8 አውሮፕላን ባሳለፍነው ዕሁድ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በረራ በጀመረ በስድስት ደቂቃ ውስጥ ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ከእምስት ወራት በፊት ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ኢንዶኔዥያ ውስጥ ተከስከሶ የ189 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የፌደራል አቪየሽን አስተዳደሩ የምርመራ ባለሙያዎችን ልኮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰከሰው አውሮፕላን አደጋ ዙሪያ ምርመራ አካሂዷል።

የአቪየሽኑ ተጠባባቂ አስተዳዳሪ ዳን ኤልዌል እንዳሉት፤ በተከሰከሱት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን እና የላየን አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ተመሳሳይ ነገሮች ተገኝተዋል።

በምርመራ የተገኘው አዲስ መረጃ በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የበረራ መንገድ ተመሳሳይነት መኖሩን ያሳያል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ50 ያላነሱ ሀገራት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ከበረራ አግደዋል።

ምንጭ፦ቢቢሲ  እና ሲኤንኤን

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም