ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ አምርተው የሰሩበትን ክፍያ ባለማግኘታቸውና ልማቱም በመቆሙ መቸገራቸውን ማህበራት ገለጹ

69
ሰመራ ግንቦት 23/2010 በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሸንኮራ አገዳ ለማቅረብ ተደራጅተው በማምረት የሰሩበትን ክፍያ ባለማግኘታቸውና ልማቱም በመቆሙ  መቸገራቸውን  በወረዳው የሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማህበራት ገለጹ፡፡ የፋብሪካው አስተዳደር  በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ  የስራ ኃላፊዎች ጋር ተቀራርበው እየሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በወረዳዉ የገበላይቱ ሸንኮር አገዳ አብቃይ ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዩሱፍ አሊ ለኢዜአ እንዳሉት ባላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት በዓመት ሁለት ጊዜ የተለያየ ሰብል በማልማት በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጾላቸው ከ2007ዓ.ም. ጀምሮ በሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማህራት አደራጅቷቸው ወደስራ በመግባት ማህበሩ  ካለው 144ሄክታር መሬት ውስጥ 60 ሄክታርን በ2008ዓ.ም. አልምተው  ምርታቸውን ለፋብሪካ አስገብተው እንደነበር  ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ላስገቡት ምርት   ክፍያ እስካሁን ባለማገኘታቸው እሳቸውም ሆኑ ሌሎች የማህበሩ አባላት ከነቤተሰቦቻቸው  ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተዋል፡፡ በውላቸው መሰረት እስከ 2010ዓ.ም. ድረስ የማልማት ግዴታ ያለበት ፋብሪካው መሬቱም ባለፉት ሶስት ዓመታት እየተጠቀመበት ባለመሆኑ በመጤ አረሞች እየተወረረ መሆኑንም ተናግረዋል ሌላው የሽንኮር አገዳ አብቃይ ማህበር አባል አቶ መሃመድ ኡመር በበኩላቸው ማህበሩ ወደ ሸንኮራ አገዳ ልማት በ2007ዓ.ም.  ሲገባ ከነበረው 146 ሄክታር መሬት ውስጥ 122 ሄክታሩ መስኖን በመጠቀም  በሸንኮራ አገዳ ተክል ቢሸፍኑም ባጋጠማቸው የውሃ ችግር  መቃጠሉን ተናግረዋል ከዚህም  በኋላ  ፋብሪካው  ስራውን በማያውቁት ምክንያት ውሉን በማቋረጡና ማልማትም ባለመቻላቸው ከ280 በላይ የማህበሩ አባላት ያጋጠማቸውን ችግር እንዲፈታላቸው ለፋብሪካውና ለክልሉ የሚመለከተው አካል ቢጠይቁም መልስ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቸውም ሆኑ የአካባቢዉ ነዋሪዎች በግፊት ሳያምኑበት ወደ ሸንኮራ አገዳ እንዲገቡ መደረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ  በወረዳው የሞሚናከሌ ሽንኮር አገዳ አብቃይ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ኖራ ኢብራሂም ናቸው፡፡ የመሬት ዝግጅት ስራው ሲከናወን ያለበቂ ሁኔታ በችኮላ በመደረጉ ቦዮች ውሃን የመሸከም አቅም ስላልነበራቸው ተበላሽተው በ2008ዓ.ም. በማህበሩ ይዞታ ላይ ተተክሎ የነበረው ከ50 ሄክታር በላይ መሬት ሽንኮራ አገዳ በውሃ እጥረት መቃጠሉን አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ100 በላይ የማህበሩ አባላት ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ከማጣታቸውም በላይ ችግሩን ለመፍታት ያደረጉት ሙከራ የፋብሪካው  አመራሮች በየጊዜው መቀያየር ምክንያት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ የተንዳሆ ሱኳር ፋብሪካ  ተወካይ አቶ ነጋሲ ሃለፎም ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ስራው የአካባቢው ህብረተሰብ ከፋብሪካው ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ቢጀመርም በውሃ ቦዮች ብልሽትና  በ2008ዓ.ም. በነበረው ድርቅ ምክንያት ያጋጠመው  የውሃ እጥረት የማህበራቱ ብቻ ሳይሆን የፋብሪካውም አገዳም ጭምር መቃጠሉን ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ስራው ያለበቂ ጥናት በመጀመሩ  በፋብሪካው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ በመድረሱ ውሉን አቋርጦ የማህበራቱ መሬት በፋብሪካው ወጪ ተዘጋጅቶ እራሳቸው የሚያዋጣቸውን ሰብል እንዲያለሙ ባለፈው ዓመት ቢሞከርም ማህበራቱ ፍቃደኛ ባለመሆናቸውን አለመሳካቱን ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን  በማህበራቱና በፋብሪካው መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት በክልሉ ከሚመለከታቸው  የስራ ኃላፊዎች ጋር ተቀራርበው እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ነኢማ መሃመድ በበኩላቸው በማህራቱና  በፋብሪካው መካከል ያለውን አለመግባበት እልባት ለመስጠት በተደጋጋሚ ቢሞከርም  የፋብሪካው አመራሮች በየጊዜው ስለሚቀያየሩ መጓተቱን አመልክተዋል፡፡ ይሁንና አሁን ካሉት የፋብሪካው አመራሮች ጋር ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት በሚቻልበት ላይ እየተወያዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዱብቲ ወረዳ ከ2ሺ በላይ አባወራዎችን አቅፈው የሚንቀሳቀሱ 16 የሸንኮር አገዳ አብቃይ ማህበራት እንደሚገኙ ኃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም