“በጦርነት ብቻ ሳይሆን በሰላም ጊዜም መስዋዕትነት ይከፈላል”

1021

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011 “በጦርነት ብቻ ሳይሆን በሰላም ጊዜም ለአገር መስዋዕትነት ይከፈላል፤ የእኔ ልጅ መስዋዕት የሆነው ለአገሩ ነው።”

ይህን ያሉት በቅርቡ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ዋና አብራሪ ካፒቴን ያሬድ ወላጅ አባት ናቸው።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓም ማለዳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን ያሳዘነ ከባድ አደጋ ገጠመው።

ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ይበር የነበረ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክሶ 157 ሰዎች ህይወታቸውን አጡ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአውሮፕላኑን ዋና አብራሪ ካፒቴን ያሬድ ጌታቸውን አባት ዶክተር ጌታቸው ተሰማን ዛሬ በአካል አግኝቶ አነጋግሯል።

ዶክተር ጌታቸው ከገጠማቸው ጽኑ ሀዘን ባሻገር ጤናቸውም ታውኳል። ይሁንና በእንባ በታጀቡ ቃላት አንደበታቸው በለሆሳስ ይናገራል።

ያሬድ ብሩህ አእምሮ የነበረው ልጅ እንደነበር የሚናገሩት አባቱ በ29 ዓመት ዕድሜው ለዋና አብራሪነት የበቃውም በዚሁ ነው ይላሉ።

“ልጄ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ ትንሹ ካፒቴን ነው። በአባትነቴ ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊነትም በጣም ሩህሩህ ልጅ ነበር። አልሆነም። ከትዝታዎቹ ጋር መኖር ብቻ ነው አማራጩ” ብለዋል።

ሆኖም ልጃቸው በጦርነትም ባይሆን በሰላም ወቅት ለአገሩ መስዋዕት መሆኑን ሲያስቡ በሀዘናቸው ውስጥ ብርታትን ያገኛሉ።

መስዋዕትነቱን ቢቀበሉትም ልጃቸው ራሱን ሳይተካ ማለፉ ሀዘናቸውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገው የሚገልጹት አባት አሟሟቱ ቢከፋም ልጃቸው ለኢትዮጵያ አፈር መብቃቱን ግን ይሁን ብለዋል።

“የምኖረው ውጭ አገር ቢሆንም ያመጣሁት ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ነው እዚሁ ኢትዮጵያ ሆኗል” ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ደውለው እንዳጽናኗቸው ገልጸው ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ልጃቸውን ጨምሮ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ወገኖች በሙሉ ለሚመጣው ትውልድ ምሳሌ እንዲሆን ማስታወሻ ቢቆምላቸው ምኞታቸው ነው።

የካፒቴን ያሬድ የቅርብ ጓደኛ ካፒቴን ቢንያም ዓለማየሁ ጓደኝነታቸው 10 ዓመታትን የዘለቀ መሆኑን ያወሳል።

“በጣም ሩህሩህ፣ ቸር፣ ችግር የሚገባው፤ በወዳጆቹ ደስታ የሚደሰት በሀዘናቸው የሚያዝን” ሲልም በሞት የተነጠቀው ጓደኛውን ይገልጸዋል።

በስራውም ታታሪና ብቃት ያለው፤ እክልም ገጥሞት የማያውቅ እንደነበር ገልጾ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማወቅ የሚያደርገው ጥረት ያስደንቀው እንደነበር ያስታውሳል።

ኢንጂነር ጥበበ ወርቁ ደግሞ የካፒቴን ያሬድ ጌታቸው አባት ጓደኛ ናቸው።

የደረሰው አደጋ የፈጠረው ሀዘን በቅርብ ላሉ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ብቻ ሳይሆን ምንጊዜም ከሁሉም ልብ የማይጠፋ፤ በመላው ዓለምም መጥፎ አሻራን ተክሎ ያለፈ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ከትናንት በስቲያ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ባልደረቦቻቸው መታሰቢያ ያደረጉ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የካፒቴን ያሬድ ጌታቸው ጓደኞች አባቱ በተገኙበት የመታሰቢያ ስነ-ስርዓት አካሂደዋል።

በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ የ35 አገራት ዜጎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶችም መጽናናትን ተመኝተዋል።