የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት ወጥነት ባለው መልኩ እየተሰጠን አይደለም— ተጠቃሚዎች

616

ሰቆጣ መጋቢት 4/2011 የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት ወጥነት ባለው መልኩ እየተሰጠ ባለመሆኑ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ተጠቃሚዎች ገለፁ።

በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የክመፅርዋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እያሱ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርቱን ሲከታተሉ ቢቆዩም ዘንድሮ በመቋረጡ መቀጠል አልቻሉም።

“በተወሰነ ደረጃ ጀምሬ የነበረው ማንበብና መጻፍ ትምህርቱን በማቋረጤ እየጠፋኝ መጥቷል” ብለዋል

በዘመናዊ አስተራረስ፣  በግልና አካባቢ ጤና አጠባበቅ ተጨማሪ ግንዛቤ እያገኙ ቢመጡም ሊቀጥሉበት  እንዳልቻሉ ተናግረዋል ።

“ከትምህርቱ የእርሻ ስራችንን በተሻለ መልኩ እንድናካሂድ ግንዛቤ እያገኘንበት ቢሆንም ወጥነት ባለው መልኩ ስለማይሰጠን የጠበቅነውን ያህል ተጠቃሚ አልሆንም ” ያሉት ደግሞ የጻግብጂ ወረዳ የምቁን ቀበሌ ነዋሪ አቶ ንጉሱ ፀሃዩ ናቸው።

ባለፈው ዓመት በተቆራረጠ መልኩ ይሰጥ የነበረው ትምህርቱ ዘንድሮ   መቋረጡን ተናግረዋል ።

የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ነጋሽ “ዘንድሮ ለወረዳው የተመደበ በጀት አነስተኛ በመሆኑ ትምህርቱን ለመጀመር አልተቻለም ” ብለዋል ።

በሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች መካከል ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር ለትምህርቱ አለመጀመር ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል ።

ኃላፊው እንዳሉት መደበኛ መምህራንን በማስተባበር ትምህርቱን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው ።

በዞኑ ትምህርት መምሪያ የጎልማሶች ጉዳይ ፈጻሚ አቶ ደርብ አለም ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የትምህርት መርሀ ግብሩ በተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር የተደገፈ ባለመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ ገልጸዋል።

ጎልማሶች በጤናና ግብርና ዘርፍ እየተሰጣቸው ያለው ትምህርት በተግባር የተደገፈ ባለመሆኑ ተጨባጭ ለውጥ እንዳላመጣ ጠቅሰዋል፡፡

መርሀ ግብሩን በበላይነት እንዲመራ የተቋቋመው ቦርድም ስራውን በአግባቡ አለመከታተሉ በዘርፉ ውጤታማ እንዳይሆን ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል ።

ዘንድሮ በዞኑ ከሚገኙ ስምንት ወረዳዎች በአምስቱ ብቻ ትምህርቱ እየተሰጠ መሆኑን አመልክተው ለመማር ከተመዘገቡ 32 ሺህ 244 ጎልማሶች ውስጥ 8ሺህ ብቻ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገበየሁ ወርቁ በበኩላቸው በቀበሌ ባሉ ባለሙያዎች በደራሽ ስራዎች በመጠመዳቸው ትምህርቱ ወጥ በሆነ መልኩ እንዳይከናወን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

” የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የግምገማ ስርዓቱ ጠንካራ አለመሆንም በዘርፉ ውጤት እንዳይመጣ አድርጓል”ብለዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ትምህርቱ በተደራጀ መልኩ እንዲሰጥ መምሪያው ኃላፊነቱን ይወጣል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነ ማሪያም  ” መርሀ ግብሩ ውጤታማ እንዳይሆን ያደረጉ ድክመቶች በግምገማ ተለይተዋል”  ብለዋል፡፡

በኮሚቴ ይመራ የነበረው የትምህርት መርሀ ግብር በትምህርት ሴክተሩ  እንደሚደረግ አመልክተው ዘንድሮ ትምህርቱ በተቋረጠባቸው ወረዳዎች አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም በአፋጣኝ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

“በየደረጃው ያሉ ስራ አስፈጻሚዎችም ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ መመሪያ ተላልፏል ”  ያሉት አቶ በሪሁን  በአተገባበሩ ላይ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ ዞን ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ 43ሺህ 401 ጎልማሶች ትምህርታቸውን አጠናቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ መረጃ ያመላክታል፡፡