ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የብቅል ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

576

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011 የፈረንሳዩ ማልተሪዬስ ሶፍሌት ኩባንያ በኢትዮጵያ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ10 ሄክታር መሬት ላይ የብቅል ማምረቻ ኢንዱስትሪ ሊገነባ ነው።

ግንባታው በአንድ ዓመት ጊዜ ተጠናቆ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2020 ብቅል ማምረት ይጀምራል ለተባለው ፋብሪካም ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

ይሄው ማልተሪዬስ ሶፍሌት የተባለው ኩባንያ በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በኋላ ብቅል ለማምረት የ 70 ዓመት ሊዝ ውል የተፈራረመው ባለፈው ዓመት ሰኔ 2010 ዓ.ም ነበር።

ኩባንያው በወቅቱ 50 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል እንደሚኖረውና ምርት ሲጀምር በዓመት 60 ሺህ ቶን ማምረት እንደሚችል ተገልጾ ነበር ስምምነቱ የተፈረመው።

የማልተሪዬስ ሶፍሌት ኩባንያ የቦርድ ሊቀመንበር ጃን ማይክል ሶፍሌት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን ቶን የሚገመት ገብስ የምታመርት መሆኗ ለኩባንያው ተመራጭ ሆናለች።

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ከውጭ ለሚገባው ብቅል የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በግማሽ ከመቀነሱም በተጨማሪ ከ 20 ሺህ  በላይ ለሚሆኑ ገብስ አምራች አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ይፈጥራልም ብለዋል።

የኩባንያው ምርት ሙሉ ለሙሉ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚውል የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ ለኢትዮጵያም  ብቅል ከውጭ የሚያስገቡ የቢራ ፋብሪካዎች 70 በመቶ ወጭ ይቀንሳልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ በቂ የውሃ አቅርቦት፣ የሰው ሃይልና በአካባቢው በርካታ የገብስ አምራች አርሶ አደሮች መኖራቸው ስራውን በአግባቡ ለማቀላጠፍ ያግዛልም ብለዋል።

ኩባንያው ምርት ሲጀምር 60 ሺህ ቶን ብቅል እንደሚያመርትና በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር እስከ 110 ሺህ ቶን ብቅል ያመርታል ነው ያሉት ሊቀመንበሩ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሀና አርዓያስላሴ ኩባንያው ብቅል ከማምረትም ባለፈ ከ 40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ገብስ አምራች አርሶ አደሮች የገበያ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ማልተሪስ ሶፍሌት ኩባንያ በኢትዮጵያ ስምምነት የተፈራረመው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ 2016 እንደነበር የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሯ፤ በተያዘለት ጊዜ ስራውን እንዲጀምር ክትትል ይደረጋልም ብለዋል።

የምርት ሂደቱን የተሳለጠ ለማድረግም የብዙ ባለድርሻ አካላትን ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ከግብርና ሚኒስቴርና ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።