የአማራ ክልል ወጣቶች ሰላምን በማስጠበቅና ለውጡን ለማስቀጠል እንዲተጉ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አሳሰቡ

67

ጎንደር መጋቢት 4/2011 የአማራ ክልል ወጣቶች ሰላምን በማስጠበቅና ለውጡን ለማስቀጠል መትጋት እንዳለባቸው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ አሳሰቡ፡፡

አቶ ምግባሩ በጎንደር ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ እንዳሳሰቡት ወጣቶች አንድነት በመፍጠር ወጣቶቹ ከሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ጋር በመሆን ለሰላምና ዕድገት ሚናቸውን መጫወት አለባቸው፡፡

ወጣቶች የክልሉን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅና ለዘላቂ ሰላም ሚናቸው ጉልህ መሆኑን የተናገሩት አቶ ምግባሩ፣ኅብረተሰቡን በሙያቸው ማገልገል ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

አንድነታቸውን የሚያላሉና የሕግ የበላይነትን የሚጥሱ ተግባራትን በመከላከል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ከማዕከላዊ ጎንደር የመጣው ወጣት ኃይለማርያም አሻግሬ የወጣቱን አደረጃጀት መደገፍና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግሯል።

በልማትና ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ኃላፊነት መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግለት  ይገባል ብሏል፡፡

የምዕራብ ጎንደሩ ወጣት አለባቸው መኮንን በበኩሉ የክልሉ ወጣቶች ከሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ጋር መርህን መሠረት ያደረገ ግንኙነት መፍጠር እንደሚያሻ አመልክቷል፡፡

''በክልል ደረጃ ያለውን የአመራር ሪፎርም እስከ ወረዳ ድረስ በማውረድ ከወጣቱ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሰራ አመራር ሊመረጥ ይገባል'' ያለው ደግሞ ከደቡብ ጎንደር የመጣው ወጣት ፈቃደአብ ወርቁ ነው፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ግምገማ ተደርጎባቸው ከአመራርነታቸው የተነሱ ግለሰቦችን የሌላ ተቋም ኃላፊ አድርጎ መመደብ እንደማይገባም አመልክቷል፡፡

መድረኩ ጎንደር ከተማን ጨምሮ ከማዕከላዊ፣ ሰሜን፣ ደቡብና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ከተወጣጡ 600 በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም