ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኮሚሽን ከ“ተጋላጭ አገራት ዝርዝር” እንዲያወጣት ጠየቀች

53

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011 ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኮሚሽን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ብሎ ከጠቀሳቸው የሶስተኛ ዓለም አገሮች ዝርዝር እንድትወጣ ጥያቄ ቀረበ።

ኮሚሽኑ ከአንድ ወር በፊት ኢትዮጵያን ጨምሮ 23 ታዳጊ አገሮች ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን በመከላከል  ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል።

ይሁንና አሁን በኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ያለው አዲስ የመንግሥት አስተዳደር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያ ከዝርዝሩ መካከል እንድትወጣ መንግስት የአውሮፓ ኮሚሽንን ጠይቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በ2010 ዓ.ም ስራውን የጀመረው አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀል ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራ ነው። በርካታ ተጨባጭ እርምጃዎችንም ወስዷል።

መንግስት በፋይናንስና በዳኝነት አካላት ላይ ከፍተኛ የለውጥ ሥራ ተግባራዊ በማድረግ መሆኑን መግለጫው አመልክቶ፤ በተለይ ስትራቴጂያዊ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑንም ነው የገለጸው።

በኢትዮጵያ የባንክ ማጭበርበር፣ የሳይበር ጥቃትና በሕገ-ወጥ መልኩ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል መስተዋሉን አስታውሶ፤ አዲሱ መንግሥት ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር መረብን በመከታተልና በመቆጣጠር በወንጀለኞቹ ላይ ጥብቅ የፋይናንስ እገዳ እየተደረገ መሆኑንም ገልጿል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ከአውሮፓ ኮሚሽን አባል አገሮችና ከሌሎች መንግሥታት ጋር በመተባበር የአገሪቷን የፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም የጠቅላይ አቃቤ ህግን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑም ተመልክቷል። 

በዚህም ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን ሕገ-ወጥ የገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን በመከላከል ዝቅተኛ አፈጻጸም አላቸው ብሎ ከዘረዘራቸው አገሮች እንድትወጣ መንግስት ጠይቋል።

በርካታ ገንዘቦች ከአህጉሪቷ ውጪ በሌሎች አገሮች እንደሚደበቅ የገለጸው መግለጫው፤ አውሮፓ ኮሚሽንም እነዚህን አካላት በማጋለጥ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም