የአይሮፕላኑ የመከስከስ አደጋና የአየር መንገዱ ገጽታ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እይታ

966

በኢዜአ ሞኒተሪንግ

ንብረትነቱ የኢትዮዽያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በበረራ ቁጥር 302 የአውሮፕላኑ ሰራተኞችን ጨምሮ 157 መንገደኞችን አሳፍሮ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ ሳለ ቢሾፍቱ አቅራቢያ ግምቢቹ በሚባል አካባቢ ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ መላው ተሳፋሪዎች መሞታቸውን ያረዳንን ዜና የሰማነው ባለፈው እሁድ ጠዋት ነበር። በርካቶችን በመሪር ሃዘን ውስጥ እንዲወድቁ ያደረገን አደጋ አየር መንገዱ አስተናግዷል። ክስተቱ ዜጎቻቸውን ሰለባ ካደረገባቸው 35 ሃገራት ህዝቦችም ባለፈ መላው አለምን በሃዘን ድባብ ውስጥ እንዲቆዩ ያደረገ ነበር።

ከአውሮፕላኑ መከስከስ አደጋ በኋላም አደጋው በተከሰተበት ቦታ በመገኘትም ሆነ ካሉበት በሁሉም የዓለማችን ማዕዘናት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ ዘገባዎቻቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ። የአውሮፕላኑን ስብርባሪ ከማሳየት በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ተሳፋሪዎችን ምስል፣ አለፍ ሲልም የቤተሰቦቻቸውን ፎቶግራፍ በማውጣት የትንታኔ ዘገባዎቻቸውን እያቀረቡ ነው።

በርካቶች ከአደጋው ጀርባ የአውሮፕላኑን ተፈጥሮአዊ የቴክኒክ ችግር እንደ ምክንያት አንስተው የትንታኔዎቻቸው አካል በማድረግ መረጃዎቻቸውን አድርሰዋል። ለዚህም  ከአምስት ወራት በፊት የተከሰከሰውና ለ189 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን የኢንዶኔዥያው ላዮን ኤይር አውሮፕላንን በአስረጂነት ያነሳሉ። እዚህ ጋር ማንሳት ግድ የሚለን ጉዳይ ቢኖር በርካቶቹ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያላቸውን የጠነከረ እምነት ነው። አየር መንገዱ ባለፉት 70 እና ከዚያ በላይ አመታት ያካበተው የደንበኞች እምነት እንዲሁም አስተማማኝ የበረራ ደህንነት በዚህ አሳዛኝ የአደጋ ወቅትም ቢሆን በመገናኛ ብዙሃኑ እይታ ሊሸረሸር አለማቻሉን ያሳያል።

አንዳንዶች ግን ከግል ፍላጎት በመነሳት በአደጋው ዙሪያ ትዝብት ላይ የሚጥላቸውን ዘገባ ይዘው ሲወጡም ታይተዋል። መሰል ዘገባዎችን የታዘበው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ፓትሪክ ጋታራ “ The racist reaction to the Ethiopian Airlines crash was all too predictable” በሚል ርዕስ ሜይል ኤንድ ዘ ጋርዲያን በተባለ የድረ ገፅ ጋዜጣ ላይ ባሰፈረው ፅሁፍ በአየር መንገዳችን ላይ ብሎም በአፍሪካውያን ላይ አንዳንድ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን የተዛባ አመለካከት አሳይቷል።

መገናኛ ብዙሃኑ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ዜጎቻቸውን ሁኔታ ብቻ በመዘገብ የሌላው ሞት ምንም እንዳልሆነ የሚያሳዩ ዘገባዎቻቸውን ሲያሰራጩ መታዘቡን ያነሳው ፓትሪክ፤ አደጋውን ተከትሎ ቲ አር ቲ በተሰኘ የቱርክ ሚዲያ የተላለፈው ዘገባ የትዝብት ግርምትን እንዳጫረበት አንስቷል። ሁኔታው እንዲህ ነው፤ ምንም እንኳ አየር መንገዱ ከአለማችን በበረራ ደህንነት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ አየር መንገድ ቢሆንም የቱርኩ ሚዲያ የዘገባ አቅራቢ እኤአ በ1996 በጠላፊዎች ተገዶ በኮሞሮስ የተከሰከሰውን አውሮፕላን በማንሳት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ደህንነት ስጋት እንዳለበት እያጋነነ ያቀርባል። ሆኖም በዜና ዘገባው ላይ በተጋባዥነት የተገኘው የአቪዬሽን ተንታኙ አሌክስ ማኬራስ ከ20 አመታት በፊት የተፈፀመ ክስተትን በመጥቀስ የአየር መንገዱን የበረራ ደህንነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ሃላፊነት የጎደለው አስተያየት ነው፤ በዚህ አይነት የአሜሪካን አየር መንገድን፣ ዩናይትድ ኤይር እንዲሁም ኤይር ፍራንስን የበረራ ደህንነት እንደ መጠራጠር ይቆጠራል፤ ሲልም ሃሳቡን እንዳጣጣለበት ፓትሪክ ፅፏል።

ፓትሪክ ሃሳቡን ለማጠናከር ከላይ የተገለፀውን ሃሳብ ብቻም አይደለም በፅሁፉ ያካተተው እውቁ የሲ ኤን ኤን የአቪዬሽን እና የቢዝነስ ዘገባ አቅራቢ ሪቻርድ ኩዌስት በአየር መንገዱ አገልግሎት ላይ የሰጠውን አስተያየት ጭምር እንጂ፤ ኩዌስት ምንድነው ያለው “ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በደንብ በተደራጀ ሁኔታ የሚመራ አየር መንገድ ነው። የደህንነት ጉዳይ እንደ ጥያቄም የሚነሳበት አየር መንገድ አይደለም፤ አፍሪካዊነቱን ሳይለቅ የምዕራባውያን አየር መንገዶች ሊሰጡት የሚችሉትን አገልግሎት እየሰጠ ያለ አየር መንገድ ነው።” እንግዲህ ኩዌስት ይህን ካለ ሌላው ትርፍ ነው ማለት ነው፤ እንደ ጋዜጠኛ ፓትሪክ ጋታታ።

መገናኛ ብዙሃኑ ከላይ የተጠቀሰውን አይነት ዘገባ ከማስተላለፋቸውም ባሻገር ከአደጋው በኋላ ያሉ አስገራሚ ክስተቶችንም ይዘው ወጥተዋል። ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ ያደረገው በረራ ለሁለት ደቂቃዎች ከተከሰከሰው አውሮፕላን በረራ እንዲዘገይ የሆነው አህመድ ካህሊድ ህይወቱ ቆይታ በሌላኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ናይሮቢ በናፍቆት ሲጠብቁት የነበሩትን አባቱን ሊያገኝ የቻለበትን እንዲሁም ባለቤቷን ከአውሮፕላን ስትወርድ እንደምታናግረው በፅሁፍ መልዕክት የስልክ ቀጠሮ የያዘችዋ ወጣት እሷም ቀጠሮዋም በአሰዛኝ ሁኔታ የውሃ ሽታ ሆነው ስለመቅረታቸውም መገናኛ ብዙሀኑ ችላ ያላሉት ጉዳይ ሆኖ አልፏል።

ከሁሉም ጉዳዮች በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት ሰዎች ባነሰም ቢሆን የአለም አቀፉ ሚዲያ መነጋገሪያ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላንን በርካታ ሃገራት ከአየራቸው ላይ እንዲወርድ እርምጃ መውሰዳቸው ነው። ነገሩን አስገራሚ ያደረገው በተመሳሳይ ቦይንግ አውሮፕላን ከአምስት ወራት በፊት አደጋ ደርሶበት ለ189 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የኢንዶኔዥያ ላዮን ኤይር አውሮፕላን አደጋ ለሃገራቱ ውሳኔ የፈየደው ነገር አለመኖሩ ነው። መሰል አደጋ ከደረሰበት ተመሳሳዩ ቦይንግ 737 ማክስ 8 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእሁዱ አደጋ በኋላ ግን ሃገራቱ አውሮፕላኑን ከአገልግሎት ውጪ እንዲያደርጉት ምክንያት ሆኗቸዋል።

ይህም የሚያሳየን አንዳች ነገር ያለ አስመስሎታል። የአየር መንገዱ አስተማማኝ የበረራ ደህንነት፣ ብቁ አብራሪዎች መኖር፣ አየር መንገዱ በየጊዜው በደንበኞች አገልግሎት ረገድ ከተለያዩ የአለማችን ተቋማት እየተሰጠው ያለው ምስክርነት ለአደጋው የአውሮፕላኑ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ለመሆኑ አውሮፕላኑ በአየር ክልላቸው እንዳይበር ውሳኔ ያስተላፉት ሃገራት የገባቸው ይመስላል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላንን ከአገልግሎት ውጪ ያደረጉ ሃገራት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት የተጠቀሰው አውሮፕላን በአየር ክልሉ እንዳይበር ውሳኔ አሳልፏል። ኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ብራዚል፣ ሲንጋፖር፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ማሌዥያ፣ አውስትራሊያ፣ ኦማን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሞሮኮ፣ ሞንጎሊያ፣ አየርላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ እና ሌሎች የፉጂ ደሴቶች እስካሁን አውሮፕላኑን ከአገልግሎት ውጭ ያደረጉ ሃገራት ዝርዝርን ተቀላቅለዋል።