በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውርፕላን ላይ አብራሪዎች ቅሬታ ያቀርቡ ነበር ተባለ

600

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011  የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በኢንዶኔዥያ ከተከሰከሰ በኋላ የተለያዩ ቅሬታዎች በአብራሪዎች ሲቀርቡበት እንደነበር ተነገረ።

ለአሜሪካኑ የፌዴራል ኤቪዬሽን ባለሥልጣን የቀረቡት ቅሬታዎች በአብዛኛው ከአውሮፕላኑ የደህንነት ሁኔታ ጋር በተገናኘ መሆኑም ተገልጿል።

አንደኛው ቅሬታ አቅራቢ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ የበረራ መመሪያው ብቁ አለመሆኑን በመጥቅስ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። 

ሌላኛው ደግሞ በአውቶ ፓይለት ሥርዓት (አውሮፕላኑን ያለ አብራሪው በሚበረው ሥልት) ዙሪያ የደህንነት ስጋት ጥያቄ መኖሩን ገልጿል ተብሏል።

ቅሬታውም አውሮፕላኑ አፍንጫውን ወደ መሬት ቁልቁል የመደፋት አዝማሚያ ያሳያል፤ ይህም የአውቶ ፓይለት ሥርዓት ችግር መሆኑን አመላክቷል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ-ማርያም የአሁኑ አደጋ ከኢንዶኔዥያው አደጋ ጋር ተመሳሳይነት አለው ብለዋል። 

በተጨማሪም “አውሮፕላን አብራሪው በረራውን ለመቆጣጠር ችግር ገጥሞት ነበር፤ ወደ መነሻውም ለመመለሰ ሙከራ አድርጓል” ብለዋል።

የአቪዬሽን ባለሥልጣኑም የቦይንግ 737 ማክስ 8 በተመለከተ መረጃዎችን እየተከታተለ መሆኑን ጠቁሞ ለአሜሪካ ብሔራዊ የስፔስ አስተዳደር ጉዳዩን እንዲከታተል መረጃ ማቀበሉን ጠቁመዋል።

የአሜሪካው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የአቪዬሽን ንዑስ ኮሚቴ የሚመሩት ቴድ ክሩዝም ባለሥልጣኑ ቦይንግ 737 አውሮፕላኖችን ከበረራ እንዲያግድ ጥሪ አድርገዋል።

“ኩባንያው ለሕዝቡ የበረራ ደህንነት ቅድሚያ መስጠት አለበት በማለትም” አሳስበዋል። 

ንብረትነቱ የኢንዶኔዥያ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የተከሰከሰው ከአምስት ወራት በፊት ነበር።